የሀገር ውስጥ ዜና

የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ስራ አስኪያጅ ተከሰሰ

By Hailemaryam Tegegn

March 27, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ማስታወቂያ በማስነገር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እናስረክባለን በማለት ከ600 ሚሊየን ብር በላይ ከተበዳዮች የሰበሰበው ፊንቴክ ኢንቨስትመንት ስራ አስኪያጅ የሆነው ዳንኤል ዮሐንስ ክስ ተመስርቶበታል።

ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 ቁጥር 1 ሀ እና ለ እንዲሁም አንቀጽ 35፣ 38 እንዲሁም የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀፅ 10 ቁጥር 1 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ነው ክስ የተመሰረተበት።

ተከሳሽ ለጊዜው ካልተያዙ ተጠርጣሪዎች ጋር በመሆን ኮምፒውተርን ወይም የኮምፒውተር ስርዓትን በመጠቀም አሳሳች ዳታ በማሰራጨት፣ የራሳቸውን በመሰወር ወይም መግለፅ የሚገባቸውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት በመጠቀም፣ ሌላውን ሰው አታልለው የተበዳይን ጥቅም የሚጎዳ ድርጊት እንዲፈፀም ለማድረግ በማሰብ ወንጀል ለመፈፀም ባደረጉት ስምምነት መሰረት የወንጀል ድርጊት መፈጸማቸውን ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አመልክቷል።

በዚህም ተከሳሽ በ2013 ዓ.ም በመጀመሪያ ሄሎ ታክሲ እና ሄሎ መኪና የተባሉትን ድርጅቶች ካቋቋመ በኋላ ድርጅቱ የታክሲ ሥራን ለማዘመን ዘመናዊ መኪኖችን ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች እና ከውጭ ሀገር በማስመጣት እንዲሁም በመገጣጠም በመንገድ እና ትራንስፖርት ባለስልጣን (ሚኒስቴር) ባወጣው መመሪያ መሰረት አሁን ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ለታክሲ ፈላጊዎች ዘመናዊ ታክሲ በዱቤ እናቀርባለን በሚል አሳሳች መረጃዎችን አሰራጭተዋል ብሏል በክሱ።

በመረጃው መሰረት ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች ተከሳሽ እና የተከሳሽ ድርጅት በተለያዩ በመንግሥት፣ በግል እና ማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨውን ማስታወቂያዎችን በመመልከት ወደ ድርጅቱ የሄዱ የግል ተበዳዮች በዱቤ ሰርታችሁ ትርፋማ የምትሆኑበትን ታክሲ ገንዘቡን በከፈላችሁት በ3 ወር ውስጥ እናስረክባቸዋለን በማለት 60 ሺህ ብር ለመመዝገቢያ፣ ከመኪናው ጠቅላላ ዋጋ 25 በመቶ ወይም 247 ሺህ 500 ብር በድርጅቱ አካውንት ላይ ገቢ እንዲያደርጉ በማድረግ የግል ተበዳዮች እምነት እንዲጥሉባችው ለማድረግ እና በረቀቀ መንገድ ወንጀሉን ለመፈፀም እንዲያመቻቸው ውል በማርቀቅ እና በድርጅቱ በተረቀቀው ውል ላይ እንዲፈርሙ ማድረግ የሚል በክሱ ላይ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ የመኪኖቻችውን ሻንሲ እና ሞተር ቁጥር ስለመጣ ፈርማችሁ ውሰዱ በማለት ከሄሎ ታክሲ ከሚል ድርጅት የሞተር እና ሻንሲ ቁጥር ላይ ፈርመው እንዲወስዱ ካደረገ በኋላ ከ600 ሚሊየን ብር በላይ ተቀብሎ መኪናውን ሳያስረክብ ድርጅቱን ዘግቶ መሰወር በክሱ ላይ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ነው።

እንዲሁም ተከሳሽ ግርማይ ገ/ሚካኤል ከተባለው (አስካል የተባለውን ድርጅት በማቋቋም በድርጅቱ ስም በ2002 ዓ.ም በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዲታደሙ ወደ ደቡብ አፍሪካ እልካቸዋለሁ በማለት ብር በመቀበል ተሰውሮ በኢንተርፖል የተያዘ) ለጊዜው ካልተያዘው ግብረ-አበር ጋር በመሆን ከዚህ በፊት ከላይ የፈፀሙትን እና ከላይ የተገለፀውን ወንጀል በሰፊው ለመፈፀም በሕጋዊ፣ በንግድ እና ውል ሽፋን ስም በተለምዶ የነጭ ኮሌታ ሳይበር አታላዮች የሚፈፅሙት ወንጀል ለመፈፀም እንዲያመቻቸው ፊንቴክ ኢንቨስትመንት ኃ/የተ/የግ/ማህበር የተባለውን ድርጅት በተሽካርከሪዎች አስመጪነት፣ በተሽካርከሪዎች መለዋወጫ፤ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን እና ጌጣጌጦች አስመጪነት እና የተሽካርከሪዎች ከአካላት እና ተሳቢዎች አስመጪነት 7 ሚሊየን ብር ካፒታል በማቋቋም ከአዲስ አበባ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ በግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም የንግድ ፍቃድ ያወጡ መሆኑ፤ ድርጅታችን የኤሌክትሪክ መኪኖችን በቀጥታ ከቻይና ቢዋይዲ ኩባንያ በማስመጣት በጠቅላላ ዋጋ 1 ሚሊየን 900 ሺህ ብር ለደንበኞች በ50 በመቶ ወይም 950 ሺህ ብር ቅድሚያ ክፍያ እና ቀሪው የ50 በመቶ በዱቤ ሽያጭ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለደንበኞች በማስረከብ ላይ ይገኛል፤ ማንኛውም ተቋም ያላደረገውን ቀሪውን 950 ሺህ ብር 50 በመቶ ያለወለድ በ5 ዓመት ውስጥ ከፍለው የሚጨርሱበት አሰራር በመዘርጋት የመኪና ባለቤት ሊያደርጋችሁ ተዘጋጅቷል፤ ስለዚህ ተመዝግበው በ3 ወር ውስጥ የመኪና ባለቤት ይሁኑ የሚሉ ማስታወቂያዎችን በማሰራት።

በኦሮሚያ ባህል ማዕከል፣ በስካይ ላይት ሆቴል፣ በመስቀል አደባባይ እና በወዳጅነት አደባባይ እንዳስረከቡ የሚያሳይ ቪድዮ እና ፎቶ በመልቀቅ እና በማሳየት እስካሁን ከ450 በላይ መኪኖችን ለተመዝጋቢዎች ያስረከበ መሆኑን፤ አሁንም ለደንበኞቻችን ለማስረከብ ወደ 400 መኪኖችን ወደ ሀገር ውስጥ እያጓጓዝን እናገኛለን፤ ኑ እና ከፍለው ቀሪውን 950 ሺህ ብር ያለወለድ እየከፈሉ የመኪና ባለቤት ይሁኑ፤ ለመኪናው ለ5 ዓመት ዋስትና እንሰጣለን፤ ድርጅታችን ከፀሐይ ኢንሹራንስ ጋር የኢንሹራንስ ውል ገብቷል፣ ከባንክ ጋር አገናኝተናል” በማለት የተለያዩ ማስታወቂያዎችን በታዋቂ ግለሰቦች፣ ታዋቂ አርቲስቶችን፣ ቲክቶከሮችን፣ የመንግሥት እና የግል ሚዲያዎችን እንዲሁም የራሳቸውን ሚዲያ ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ማስታወቂያውን በማሰራጨት በርካታ ሰዎች በተከሳሽ እና በተከሳሽ ድርጅት የተሰራጨውን ትርፋማ የምትሆኑበትን ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መኪና እናቀርባለን የሚል አማላይ እና አሳሳች ማስታወቂያዎችን በመመልከት በርካታ ግለሰቦች ወደ ድርጅቱ ሄደው በመመዝገብ ቅድመ ክፍያ 950 ሺህ ብር ከከፈሉ በኋላ በማስታወቂያ ላይ ከተነገረው ገንዘብ 950 ሺህ ብር በተጨማሪ (ተጨማሪ እሴት ታክሲ) በሚል 285 ሺህ ብር እና ለቦሎ እና ለታርጋ ተብሎ ከ130 ሺህ ብር እንዲከፍሉ አድርገዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ላይ አመልክቷል።

በአጠቃላይ 1 ሚሊየን 365 ሺህ ብር በማስከፈል በ3 ወር ውስጥ መኪና እናስረክባለን በማለት በተከሳሽ እና በተከሳሽ ድርጅት በተረቀቀው ውል ላይ እንዲፈርሙ በማድረግ እንዲሁም በ3 ወር ውስጥ መኪና አስረክባቸዋለሁ በማለት ከ1 ሺህ 430 በላይ ግለሰቦችን በመመዝገብ ከእያንዳንዱ ተመዝጋቢ ከብር 950 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 86 ሚሊየን ብር በላይ ሰብስበው 100 መኪኖችን ለራሱ፣ ግብረ-አበሩ እና የጥቅም ተጋሪ ለሆኑ ግለሰቦች ብቻ አስረክቦ ሳለ በሚዲያዎች ከ520 በላይ መኪኖችን አስረክበናል በማለት አሳሳች መረጃዎችን በመናገር ግለሰቦች ቀርበው እንዲመዘገቡ እና ገንዘብ እንዲከፍሉ ሲያደርግ ነበረ በሚል 19 ተደራራቢ ክሶች ተመስርተውበታል።

የክስ መዝገቡን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ነው።

በመቅደስ ከበደ