የሀገር ውስጥ ዜና

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በፒያሳ የተገነባውን ዘመናዊ የንግድ ሕንፃ አስመረቀ

By sosina alemayehu

March 28, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በፒያሳ ለወርቅ ንግድ ሱቆች አገልግሎት እንዲውል ተደርጎ የተገነባውን ዘመናዊ የንግድ ሕንፃ (ጎልድ ሞል) ዛሬ አስመርቋል።

የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትርና የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ እንዲሁም በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) አማካኝነት ተከናውኗል።

የ50 ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን በተለያዩ ስኬታማ ተግባራት እያከበረ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ÷ ይህንን ዘመናዊ የንግድ ማዕከል ለምረቃ ማብቃቱ ለንግዱ ማህበረሰብ በተለይም ለወርቅ ነጋዴዎች ትልቅ የምስራች መሆኑ ተመላክቷል።

በፒያሳ አዲስ ገጽታ ላይ የተገነባው የንግድ ሞሉ÷ የከተማዋን የኮሪደር ልማት ተከትሎ ለሚመጡ የንግድ ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጥና ለአካባቢው ውበት የጨመረ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑም ተገልጿል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የ50ኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ በዓሉን በተለያዩ መርሐ ግብሮች እያከበረ ይገኛል።