አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙኃን የምርጫ ቅስቀሳ ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ይፋ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሐይማኖት ዘለቀ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተደለደለው ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የ10 በመቶ ብልጫ አለው።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች የአየር ሰዓቱን ሲጠቀሙ ህገ መንግሥቱን፣ የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁንና ሌሎች ህጎችን እንዲሁም የማህበረሰብ ባህልና እሴትን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በበኩላቸው÷ ፓርቲዎች የተደለደለውን ነፃ የአየር ሰዓት በአግባቡ ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል።
ይህንን ማድረግ ለፓርቲያቸው ብቻ ሳይሆን ለመራጩ ሕዝብ የመራጮች ካርድ እንዲያወጣ መነሳሳትን እንደሚፈጥርና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲሰጡ እንደሚያግዝ አንስተዋል።
ቦርዱ ነፃ የአየር ሰዓት ድልድሉ በዕጣ እንዲሆን ማድረጉ ነፃና ገለልተኛ በሆነ መልኩ ነፃ የአየር ሰዓቱ እንዲከፋፈል የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።
ነፃ የአየር ሰዓቱና የጋዜጣ አምድ ድልድሉን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ያዘጋጀ ሲሆን÷ 782 ነጥብ 5 የሬዲዮ ሰዓት፣ 513 ነጥብ 45 የቴሌቪዥን ሰዓት እንዲሁም 576 የጋዜጣ አምድ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደልድሏል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደለደለላቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ከቅዳሜ፣ እሁድ እና የበዓላት ቀናት ውጪ ከመጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጠቀሙበት እንደሆነም ተገልጿል።
በአንዷለም ተስፋዬ