የሀገር ውስጥ ዜና

በሲዳማ ክልል 14 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ

By Mikias Ayele

March 28, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በ2018 በጀት ዓመት ያለፉት ስምንት ወራት በክልሉ ከ14 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል አሉ፡፡

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ለታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና እና ሽልማት አበርክቷል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ እንዳሉት÷ የንግዱ ማህበረሰብ ግብር በወቅቱ እና በታማኝነት መክፈሉ መንግሥት ሀገራዊ ኃላፊነቶችን በተገቢው እንዲወጣ ያስችላል።

ከክልሉ ሲመሰረት የነበረው ዓመታዊ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከ5 ቢሊየን ብር ያልተሻገረ እንደነበረ አስታውሰው÷ አሁን ላይ ከፍተኛ አቅም መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

ለአብነትም ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 14 ቢሊየን ብር  ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

የክልሉ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካይ የ40 በመቶ እድገት እያሳየ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት፡፡

የሲዳማ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ደምሴ እሳቱ በበኩላቸው÷ ባለፉት 8 ወራት የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ5 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል።

ባለስልጣኑ የዘመኑ እና በቴክኖሎጂ የታገዙ የገቢ አሰባሰብ ስልቶችን ተግባራዊ ማድረጉ ለተገኘው ውጤት  አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

በነገዎ ብዙነህ