ዓለምአቀፋዊ ዜና

የሁቲ ሁለተኛ ዙር ጥቃት እና የአሜሪካ እግረኛ ጦር…

By Hailemaryam Tegegn

March 29, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መቋጫ ያልተገኘለትን የኢራን እና አሜሪካ-እስራኤል ጦርነት በይፋ የተቀላቀለው የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሁቲ በእስራኤል ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል፡፡

ባለፉት ሰዓታት በኢራን እና አሜሪካ-እስራኤል ጦርነት ዙሪያ የወጡ መረጃዎች፡-

👉 የሁቲ ጥቃት በእስራኤል ላይ

ጦርነቱን በይፋ የተቀላቀለው የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሁቲ በእስራኤል ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል፡፡

ሁቲ በእስራኤል ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ውጤታማ የሚሳኤልና የድሮን ጥቃቶችን መፈጸሙን የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ በቀጣይ ቀናትም መሰል ጥቃቶችን እንደሚፈጽም አስጠንቅቋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

👉 የአሜሪካ እግረኛ ጦር በኢራን

አሜሪካ በኢራን የእግረኛ ጦር ልዩ ዘመቻ ለመጀመር እየተዘጋጀች መሆኑ ተነግሯል፡፡

የአሜሪካ ጦር (ፔንታጎን) በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ያሳተፈና ለሳምንታት የሚዘልቅ የእግረኛ ጦር ዘመቻ ለመጀመር ማቀዱ ነው የተገለጸው፡፡

እቅዱ እስካሁን በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይሁንታ አለማግኘቱን የሀገሪቱን ባለስልጣናት ዋቢ አድርጎ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡

👉 የኢራን ጥቃት በአልሙኒየም መሰረተ ልማቶች ላይ

ኢራን በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እና በባህሬን የአልሙኒየም መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች፡፡

የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ በተለይም የባህሬን የአልሙኒየም ፋብሪካ በአሜሪካውያን የሚተዳደርና ለአሜሪካ ጦር ወታደራዊ ቁሳቁስ የሚያቀርብ መሆኑን ገልጿል፡፡

👉 የእስራኤል አዲስ ጥቃት

እስራኤል በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ወታደራዊ የማዘዣ ጣቢያዎችና የጦር መሳሪያ ማምረቻ መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች፡፡

የእስራኤል ጦር ከቴህራን በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም መሰል ጥቃቶችን መፈጸሙንና ከፍተኛ የኢራን ወታደራዊ ባለስልጣናትን ኢላማ ማድረጉን ገልጿል፡፡

👉 የሰላም ጥረት በፓኪስታን

ፓኪስታን አንድ ወር ያስቆጠረውን የኢራን እና አሜሪካ-እስራኤል ጦርነት ለማስቆም የጀመረችውን ጥረት ቱርክዬ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ግብጽ ተቀላቅለዋል፡፡

የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰላም ጥረቱ ላይ ለመምከር በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸውን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ