የሀገር ውስጥ ዜና

ውጊያን በሩቅ የሚያስቀርና በአጭር ጊዜ ተዋግቶ የሀገሩን ጥቅም የሚያስከብር ሠራዊት ተገንብቷል – ሌ/ጄ ሹማ አብደታ

By Melaku Gedif

March 29, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠላቶቿን እያንበረከከች በክብር የኖረችው ኢትዮጵያ ዛሬም በልጆቿ ተከብራ ትኖራለች አሉ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ፡፡

ሌ/ጄ ሹማ አብደታ በግዳጅ ቀጣና ተዘዋውረው ከሠራዊቱ ጋር ባደረጉት ውይይት አጠቃላይ ስለሀገራዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ጠላቶቻችን የኢትዮጵያን ዕድገት በሴራ ለማቀጨጭ ቢሞክሩም ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ከፍታቸውን ማረጋገጣቸው የማይቀር ጉዳይ ነውና ጠላቶች ተስፋ ሊቆርጡ ይገባል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውጊያን በሩቅ የሚያስቀር ካልሆነ ደግሞ በአጭር ጊዜ ተዋግቶ የሀገሩን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር ሠራዊት መገንባቷን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ የሕዝቦቿን ኑሮ እንዳትለውጥ ፅንፈኛ፣ ሸኔና ሌሎች ቡድኖች ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብረው ቢሠሩም ቅዠታቸው በሠራዊቱ እንደጉም መበተኑን ገልፀዋል።

ሠራዊቱ የሠላምና የልማት ፀር የሆኑ ቡድኖችን የመመንጠሩን ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል የሀገሩን ዕድገት እና የሕግ የበላይነት በዘላቂነት ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የትኛውንም ዓይነት ግዳጅ በየትኛውም ቦታና ጊዜ የመፈፀም አቅሙን ከጊዜ ወደ እያሣደገ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

ይህም በዝግጁነትም ሆነ በውጊያ አቅሙ ጠንካራ መሆኑን የሚያመላክት ነው ማለታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡