ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኢራን በእስራኤል የኢንዱስትሪ ማዕከል ላይ የሚሳዔል ጥቃት ፈጸመች

By abel neway

March 29, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን በደቡባዊ እስራኤል በሚገኝ የኢንዱስትሪ ማዕከል ላይ የሚሳዔል ጥቃት ፈጽማለች፡፡

የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው÷ ቴህራን በኢንዱስትሪ ማዕከሉ ላይ በፈጸመችው የሚሳዔል ጥቃት የኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ በእሳት ተያይዟል፡፡

የእስራኤል ብሄራዊ የእሳት አደጋ መከላከል አገልግሎት በኬሚካል ፋብሪካው ላይ የደረሰውንና በከፍተኛ ሁኔታ የተያያዘውን እሳት ለማጥፋት ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡

ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ የሚገኙ ሠራተኞች አና ነዋሪዎችም ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲጠለሉ አሳስቧል፡፡

ኢራን አሜሪካና እስራኤል ለሚፈጽሙባት ጥቃት አጸፋ በአካበቢው በሚገኙ የዋሽንግተን አጋር ሀገራት ቁልፍ ተቋማት ላይ ጥቃት እየፈጸመች መሆኗንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ እስራኤል በኢራን ወታደራዊ የማዘዣ ጣቢያዎች እና የጦር መሳሪያ ማምረቻ ማዕከላት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሟ አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል ኢራን ከሰሞኑ በሳዑዲ ዓረቢያ በፈጸመችው ጥቃት የአሜሪካ ወደታራዊ ጄት ተመትቶ መውደቁ መረጋገጡን ዘገባው አመልክቷል፡፡

በመላኩ ገድፍ