አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳ ለደረሰባቸው ወገኖች የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በተጨማሪም የባንኩ ወላይታ ሶዶ ዲስትሪክት 1 ሚሊየን ብር እንዲሁም የባንኩ ሠራተኞች ማኅበር 500 ሺህ ብር በድምሩ 11 ሚሊየን 500 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ አልሰን አሰፉ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት÷ ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከዞኑ ሕዝብና መንግሥት ጎን በመቆም ላሳየው አጋርነት ምስጋና ማቅረባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።