አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጡ እውን መሆኑን ተከትሎ በርከታ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጸኑ ጉዳዮች ታይተዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ያልነበሩ አዳዲስ ልምምዶች ተስተውለዋል።
በተለይም በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ ይንጸባረቅ የነበረው ጽንፍ የረገጠ እሳቤ እንዲረግብ የሚያስችሉ ወሳኝ ርምጃዎች በመወሰዳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር መስራት የሚችሉበት ዐውድ ተፈጥሯል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ‘ተቃዋሚ’ በሚል በመጥራት የማራቅ እና የመግፋት ዝንባሌን ለመለወጥ ‘ተፎካካሪ’ በሚል ከማረም ጀምሮ ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችል ጥርጊያ ተበጅቷል።
ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን በጋራ እንፍታ የሚል የመሪ ጥሪ የታየውም በዚህ የለውጥ ጊዜ መሆኑን ልብ ይሏል።
ሀገራዊ ለውጡ ዜጎችን ወደ ፊት ያመጣና ተሣትፏቸውን ከፍ ያደረገ እንዲሁም የፖለቲካ ባይተዋርና ባለቤት የሚለውን ክፍፍል አስቀርቷል።
ይህንን ጉዳይ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ዘንድ ያየን እንደሆነ፤ የዳር እና የመሐል በሚል የነበረውን የክፍፍል ግንብ አፍርሶ የአንድነት ድልድይ ገንብቷል።
በዚህም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ‘የዳር እና የመሐል’ የሚል ክፍፍል ውስጥ ሳይገቡ ለሀገራቸው አስተዋጽኦ የሚያበርክቱበት እና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ መደላድል ተፈጥሯል።
ለውጡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገራዊ ጉዳይ ያገባዋል የሚለውን ዕሳቤ በማምጣቱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት የድርሻቸውን እንዲወጡ ዕድል ፈጥሯል።
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራት ለመጠገን በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሉም ወገን ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆን የተደረገው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚቀርበውን ተደጋጋሚ ጥሪ በአብነት ማንሳት ይቻላል።
በጥሪው መሰረት ለዓመታት ኑሯቸውን በውጭ ያደረጉና ለሀገራቸው ባይተዋርና የነበሩ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ገብተዋል፣ በሚመቻቸውና በሚፈልጉ የፖለቲካ አደረጃጀት ተሰልፈዋል እንዲሁም ለሀገራቸው ዕድገት ሐሳባቸውን አዋጥተዋል።
በተለያዩ ሀገራትና ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ፊት የመጡበት፣ መደራጀት፣ ቢሮ መክፈት እንዲሁም ሐሳቦቻቸውን ወደ ሕዝብ ማቅረብ መጀመራቸውም በለውጡ ዓመታት የታየ የፖለቲካ ዐውድ መለወጥ አብነት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህንን ጉዳይ በተመለከተም ሲገልጹ፤ የፖለቲካ ምህዳርን መክፈት በ2010 ዓ.ም የወሰንነው ቁልፍ ውሳኔ ነው ይላሉ።
ከኖረው ፓርቲዎችን ተቃዋሚ አድርጎ ከመመልከት ህጋዊ ተፎካካሪዎች አድርጎ በማስተናገድ ዴሞክራሲያዊ ከባቢን ለመፍጠር መሰራቱን በመጥቀስ፤ ይህ የአስተሳሰብ ሽግግር ሰላማዊ የፉክክር ባሕል ለኢትዮጵያ መፃዒ ተስፋ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ላይ የተመሠረተ እንደነበር ያብራራሉ።
በዚሁ አቋም በመመራት ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተመዘገቡ ፓርቲዎች ጋር ተከታታይ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል።
በአቢይ ጌታሁን