አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ሕጋዊነታቸው የተቋረጠባቸው በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
ባለሥልጣኑ ከትምህርት ዘርፉ እንዲወጡ የተወሰነባቸውና ውሳኔውን ያልተገበሩ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ሕጋዊነታቸው መቋረጡን አመልክቷል።
የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በተከናወነ የክትትልና ቁጥጥር ስራ የዳግም ምዝገባ ስርዓት ውስጥ ባለመግባታቸው ምክንያት ከከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እንዲወጡ የታዘዙና ውሳኔውን ተግባራዊ ያላደረጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
በተደጋጋሚ ጊዜያት ለተቋማቱ ጥሪ ቢቀርብላቸውም የሚጠበቅባቸውን ሂደት በማሟላት ከትምህርት ዘርፍ አለመውጣታቸውን ገልጿል።
በመሆኑም ተቋማቱ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ህጋዊነታቸው መቋረጡን አመልክቷል።
በዚህም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ተሰማርተው ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት እንዳይሰጡና እንዲከለከሉ ለሁሉም ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤቶች፣ የከተማ መስተዳድር ከንቲባ ጽ/ቤቶች፣ ፍትህ ቢሮዎች፣ ፖሊስ ኮሚሽን ጽ/ቤቶች፣ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጽ/ቤቶች እና የክልል እና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች ጠይቋል።
በተጨማሪም እስካሁን ያደረሱት ጉዳት ካለ በመፈተሽ አስፈላጊ የሕግ እርምት ርምጃ እንዲወሰድባቸው ባለስልጣኑ አሳስቧል።