የሀገር ውስጥ ዜና

ከአይናፋርነትን የተላቀቀው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ

By Mikias Ayele

March 30, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት በማድረግ የባህር በር ጥያቄን አጀንዳ አድርጓል።

 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነትን ከማስከበር፣ የኢኮኖሚ ልማትን ከማፋጠን እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከመገንባት አንፃር በለውጡ ዓመታት በርካታ ስኬቶች አስመዝግቧል።

የለውጡ መንግሥት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በወሳኝ የዲፕሎማሲ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ውጤቶችም ማስመዝገብ ችሏል፡፡

በተለይምበ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ ቅድሚያ ለጎረቤት፣ የቀጠናዊ ትስስርን እንዲሁም የዓለም አቀፍ ትብብር የሚደግፍ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ የኢትዮጵያን ተሰሚነትና ቅቡልነት ከፍ ያደረጉ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ግንኙነት ረገድ ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ፣ ከአይናፋርነት የተላቀቀ እና ጥበብና ድፍረት የተሞላበት አካሄድን በመፍጠር የኢትዮጵያን ተፈጥሮ ሀብቶች ማልማትን ጨምሮ የባህር በር ጥያቄ አጀንዳ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

በተለይ ፍትሐዊው የባህር በር ጥያቄ ወሳኝ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ እንዲሆን በማድረግ ጥያቄው በተለያዩ ሀገራት መንግሥታት እንዲሁም በባለብዙ ወገን ተቋማት ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግም ተችሏል፡፡

በቅድሚያ ለጎረቤት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት በስጋት የሚታዩ ጎረቤት ሀገራትን ወዳጅ እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ በርካታ ቀጣናዊ ኢኒሼቲቮች ተቀርጸው ተተግብረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካ ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነትን በመፍጠር በትብብር እየሰራች ሲሆን፤ በቀጣናው ያላትን የመሪነት ሚና በአግባቡ እየተወጣች ትገኛለች፡፡

በተመሳሳይ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ጫና እና የእጅ አዙር ጥቃቶችን በመቋቋም ብሔራዊ ጥቅምን ማሳካት የቻለችበት፣ እንደ ብሪክስ ያሉ ትብብሮች ላይ አባል የሆነችበት፣ ጠንካራ ወዳጅ ሀገራትን ያፈራችበት አመት ነው፡፡

እንደ ተባበሩት መንግስታት ባሉ ተቋማት አፍሪካውያን በባለ ብዙ ወገን ተቋማት ውክልና እንዲኖራቸው  ድምፅ የሆነችበት እንዲሁም ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን መርህ በተግባር ያሳየችበት ጊዜም ነው፡፡

በሚኪያስ አየለ