አካል ጉዳተኞች ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች እኩል ተገቢው የዴሞክራሲ ተሳትፎና ውክልና እንዲኖራቸው በተለየ ሁኔታ ትኩረት ያሻቸዋል፡፡
ስለሆነም የእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁኔታ በተገቢው ተጠንቶ የመራጮች ትምህርት እንዲያገኙ፣ በመራጭነት/ተመራጭነት እንዲመዘገቡ እና እንዲመርጡ የሚያስችል እቅድ ወጥቶ ይተገበራል፡፡
አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያፀደቀችው ዓለም ዓቀፍ የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽን፤ የአካል ጉዳተኞች በፖለቲካው መስክ በነፃነት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸው አማካኝነት በመምረጥና በመመረጥ ከሌሎች ጋር ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚኖርባት ይደነግጋል፡፡
በዚህ ረገድ:- 👉የምርጫ አሰራሮች፤ 👉ቁሶችና ስፍራዎች ለአካል ጉዳተኞች ተስማሚ እንዲሆኑ፤ 👉ድምጻቸውን በነፃነትና በምስጢር የሚሰጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ 👉እርዳታ የሚሹ በሚመርጡት ሰው የመታገዝ መብት እንዲኖራቸው ፤ 👉ተመርጠው በማናቸውም ደረጃ የማገልገል ዕድል እንዲኖራቸው ፤ 👉አስፈላጊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ የአካል ጉዳተኞች ያለአድልዎ ከሌሎች ጋር በእኩልነት በፖለቲካና እና በህዝብ አስተዳደር ጉዳዮች እንዲሳተፉ ማድረግና ማበረታታት ያለበት መሆኑ በኮንቬንሽኑ አንቀፅ 29 ሥር ተደንግጓል፡፡
የምርጫ አዋጅ ቁ. 1162/2011 መሠረትም በምርጫ ወቅት የኮንቬንሽኑ አንኳር ድንጋጌዎች ተፈፃሚ የሚሆኑበትን ሥርዓት ዘርግቷል፡፡
አዋጁ የአካል ጉዳተኞች የጉዳት ዓይነት በመራጮች መዝገብ ላይ እንዲገለፅ ከማድረግ አንስቶ ለዕጩነት ለመቅረብ የሚያስፈልገው የድጋፍ ፊርማ ብዛት ከሌሎች ዕጩዎች ያነሰ እንዲሆን ያዝዛል፡፡
እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ ከፍ እንዲል እነርሱን በአባልነት፣ በዕጩነት እና በአመራርነት ለሚያሳትፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግበት የማበረታቻ ሥርዓት ዘርግቷል፡፡