አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትና ዓለም አቀፍ ቀውስ ምክንያት በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)።
ሚኒስትሩ በመካካለኛው ምስራቅ ያለው ጦርነትና አለመረጋጋት በሀገራችን የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ እንዲሁም መንግሥት የሚከተላቸውን አቅጣጫዎች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን የሚከታተል፣ ርምጃ የሚወስድና የነዳጅ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች የሚለይ ልዩ ክፍል መቋቋሙንም ይፋ አድርገዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ጦርነትና አለመረጋጋት በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
በጦርነቱ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጦርነቱ በፊት የአንድ በርሜል ነጭ ናፍጣ ዋጋ 80 ዶላር የነበረ ሲሆን÷ አሁን 230 ዶላር መድረሱን ቤንዚንም ከ70 ወደ 150 ዶላር ማሻቀቡን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር የነበራት የረጅም ጊዜ የነዳጅ ግብይት ውል በጦርነቱ ምክንያት መስተጓጎሉንና አቅራቢ ሀገራቱ ምርቱን ማቅረብ እንደማይችሉ ማሳወቃቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም ምክንያት በግዥ ሂደት ላይ የነበረ ከ180 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ አለመቅረቡን ጠቅሰዋል።
በጦርነቱና አለመረጋጋቱ ምክንያትም በነጭ ናፍጣ ላይ የነበረው የቀን አቅርቦት ከ9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር ወደ 4 ነጥብብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዝቅ ማለቱን ጠቁመዋል።
የተለያዩ ሀገራት ያጋጠማቸውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ተከትሎ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እቀባዎችን እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፥ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው መርህ ግን ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ችግሩን በጋራ ለመሻገር መሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግሥት የተፈጠረውን የአቅርቦት እጥረት ለመቅረፍና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይገቱ ነዳጅን ከተጓዳኝ ገበያ ስለሚገዛና የዓለም የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት በሦስት እጥፍ ዋጋ እየገዛ ለማቅረብ መገደዱን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለመታደግ በአሁኑ ወቅት በነጭ ናፍጣ ላይ በአንድ ሊትር 95 ብር በቤንዚን ላይ ደግሞ 42 ብር ድጎማ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
እስካሁን 262 ቢሊዮን ብር ገደማ ድጎማ ማድረጉን በማንሳት በየወሩም ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ብር ለድጎማ እየተመደበ መሆኑ ጠቅሰዋል።
ያጋጠመው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በሀገርና በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳያሳድርና በፍትሐዊነት ለመምራት መንግሥት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የቅድሚያ አሰጣጥ ውሳኔ ማሳለፉን ይፋ አድርገዋል።
በዚህም መሠረት 1. ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በማደያ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፣ 2. ከፍተኛ አምራችና የኤክስፖርት ድርጅቶች በቀጥታ፣
3. ልዩ ትኩረት የሚሹ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች በቀጥታ፣ 4. የገቢና ወጪ ንግድን ጨምሮ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች
5. ግብርናን የሚያዘምኑ ትራክተሮች፣ 6. የከተማና ሀገር አቀፍ የብዙሃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች
7. እንዲሁም በናፍጣ የሚሰሩ ሌሎች ለህብረተሰብ ግልጋሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርግ የቅድሚያ የነዳጅ አጠቃቀም አሠራር የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ውጭ የሚደረግ የነዳጅ ስርጭት ተገቢ ባለመሆኑ እርምጃ ይወሰዳል ያሉት ሚኒስትሩ÷ ይህንን ውሳኔ በአግባቡ ለማስፈጸም በቅንጅት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል መንግሥት የፌደራልና የክልል ተቋማትን ያካተተና ስርጭቱን 24/7 የሚከታተል የሁኔታዎች ልዩ የመከታተያ ክፍል ማቋቋሙን ይፋ አድርገዋል።
ልዩ የመከታተያ ክፍሉ በማዕከል የሚመራ ሲሆን÷ የነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭትና አጠቃቀምን የሚከታተል፣ ውሳኔዎችን የሚየቀርብና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የሚለይ መሆኑን ተናግረዋል።
በነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ዙሪያ ሕገ-ወጥ ድርጊት የፈጸሙ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ 658 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን÷ ከ720 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተይዞ ለመንግሥት ገቢ ሆኗል ብለዋል።
ከሕብረተሰቡ የሚከጠበቁ ተግባራትን ይፋ ያደረጉት ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ በዚህም መሠረት፦
1) ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀም፣ 2) የታዳሽ ኃይል አማራጮችን የመጠቀም ስልትን መከተል፣
3) የእግር ጉዞ ባህልን ማጎልበት 4) አላስፈላጊ የጉዞ ፕሮግራሞችን መሰረዝና ማቆም
5) የሕዝብ ትራንስፖርትን መጠቀም 6) በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ረገድ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።