አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2010 ዓ.ም እውን የሆነውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ የመጣው መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተቋማት ግንባታን ለሀገረ መንግሥት ግንባታው ምሰሶ በማድረግ ባለፉት ስምንት ዓመታት አመርቂ ስራዎችን አከናውኗል።
በተለይም የፀጥታ እና የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም ለዚህ ትልቅ ማሳያ ሲሆኑ÷ በዚህም ከለውጡ ወዲህ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ሪፎርም ኢትዮጵያ ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር የሚያስችል መሰረት ጥሏል።
ተቋማቱ በአመራርና በሰው ኃይል የተጠናከሩ፣ አቅማቸው በቴክኖሎጂ የበለፀገ፣ በደኅንነት መሰረታዊና አንኳር ክህሎቶች የፈረጠሙ እና በዴሞክራሲያዊ መሰረት ላይ የታነፁ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል።
በውጤቱም ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም የቆሙ፣ ወገንተኝነታቸው ለህግ ብቻ የሆኑ፣ ጠላቶች ኢትዮጵያ ላይ ፈፅሞ ክፉ እንዳያስቡ የሚያደርጉ፣ ለሀገር ጋሻ እና ጥላ የሆኑ ተቋማት ተገንብተዋል።
በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች በዘርፉ የሚስተዋሉ ስጋቶችን ከመቀልበስ ባሻገር ቀድሞ ችግሮችን በመለየትና አዝማሚያዎችን በመተንተን ድንገተኛ የሚባሉ የደኅንነትና የፀጥታ ክፍተቶችን ማስቀረት እየተቻለም ይገኛል።
በተጨማሪም ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት በተደረገው ሪፎርም ውትድርና ጀግኖች የሚመርጡት ለሀገር ሉዓላዊ አንድነት ዋጋ የሚከፈልበት የተከበረ ሙያ መሆን ችሏል።
በዚህም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዘመናዊ ትጥቅን በማሟላት የሀገርን ተጋላጭነት ማስቀረት የሚችል አስተማማኝ ኃይል ማድረግ ተችሏል።
ለዚህም የሆሚቾ ጥይት ፋብሪካ እና የድሮን ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርተው ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ በመገንባት ስራ መጀመራቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሰራዊቱ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት የተዋቀረና ለሀገር ሉዓላዊነት ዘብ የቆመ የመጨረሻው ጠንካራ ምሽግ በመሆን ባለፉት ዓመታት በነበሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መልከ ብዙ ግዳጆችን በብቃት በመወጣት በአደረጃጀት፣ በትጥቅ፣ በአስተሳሰብና ስልጠና ነጥሮ የወጣ ዘመናዊ ሠራዊት ሆኗል።
በኢትዮጵያ ላይ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጣ ጥቃትን ከሩቅ የሚያስቀርና የሚመክት የምድር ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የሜካናይዝድ፣ የባሕር ኃይል፣ የልዩ ዘመቻ እና የሳይበር ኃይል መገንባቱም ተገልጿል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተቋሙ የተሰራው ሪፎርም በርካታ ውጤቶች ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ ሀገራችን በታሪኳ በዚህ ደረጃ ብዛትና ጥራት ያለው የፕሮፌሽናል ሰራዊት ገንብታ አታውቅም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ÷ ሀገሩንና ሙያውን የሚወድ የሚሰጠውን ግዳጅ በአነስተኛ ኪሳራ የመፈፀም ብቃት ያለው ኃይል ተገንብቷል ብለዋል።
በተገኙ ድሎች ባለመኩራራት የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ድሎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ መግለፃቸውም ይታወሳል።
በአድማሱ አራጋው