የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና የቀጣናውን ሰላም የሚያስጠብቅ አስተማማኝ ሠራዊት ተገንብቷል

By Hailemaryam Tegegn

March 31, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን ክብር፣ ብሔራዊ ጥቅምና የቀጣናውን ሰላም የሚያስጠብቅ አስተማማኝ ሠራዊት ተገንብቷል አሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)።

ጠንካራና አስተማማኝ የጸጥታና ደህንነት ተቋማትን መገንባት ከሀገራዊ የሪፎርም አምዶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው፥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ተቋማዊ አውዶች ሰፊ ሪፎርም አድርጓል ነው ያሉት።

ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጣ ጥቃትን የሚመክት ብቁ የምድር ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የሜካናይዝድ፣ የባሕር ኃይል፣ የልዩ ዘመቻና የሳይበር ኃይል መገንባቱን አስረድተዋል።

በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀትና በውጊያ ቴክኖሎጂ ጠንካራ ተቋማዊ ቁመና መፈጠሩን ያነሱት ሚኒስትሯ፥ ግዳጁን በላቀ ብቃት የሚወጣና ጦርነትን በሩቁ የሚቀለብስ አስተማማኝ ሠራዊት መገንባት ተችሏል ብለዋል፡፡

ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ የውጊያ ቴክኖሎጂ የሚጠቀምና በአግባቡ የሚመራ ብቁ የሰው ኃይልን የማብቃት ሥራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በወታደራዊ መሣሪያዎች ራስን ለመቻል የተያዘውን ሀገራዊ ግብ በማሳካት ረገድ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ተቋማት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡

በተሰማራበት ቦታ ሁሉ የሰላም ማስከበር ግዳጆችን በብቃት በመወጣት ለቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ተፈላጊ ሠራዊት መሆኑን በተግባር አስመስክሯል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በለውጡ ዓመታት በአቅም፣ በዲሲፕሊን፣ በስነ ልቦና እና ከየትኛውም ወገንተኝነት ነጻ ሆኖ ለሕገመንግሥቱና ለሀገር ሉዓላዊነት ብቻ የሚቆም ኢትዮጵያዊ ሠራዊት መገንባቱን ገልጸዋል፡፡