አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ባለፉት ስምንት ወራት በተደረገው ቁጥጥር በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 1 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ ተይዟል አሉ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የስምንት ወራት አፈፃፀም ገምግሟል።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታ እና ሌሎች ምክንያቶች የነዳጅ ፍላጎትና ፍጆታ ጨምሯል።
በመሆኑም ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ነዳጅ ከውጭ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል።
ነዳጅ እንዳይባክን እና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ለማስቻል የቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት ስምንት ወራት በተደረገው ቁጥጥር በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 1 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ ተይዟል ብለዋል።
ከህገ ወጥ ድርጊቱ ጋር በተያያዘ 658 ሰዎች ላይ ህጋዊ ርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት በኩል ያሉ ህገወጥነትን ከመከላከል ጎን ለጎን የነዳጅ አጠቃቀምን በተመለከተ የተወሰኑ ልዩ ውሳኔዎችን መተግበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አክለውም ከሆርሙዝ ሰርጥ ጋር በተያያዘ ችግር ከተፈጠረ በኋላ በተለያዩ መንገዶች ከመርከቦች ነዳጅ በመግዛት 3 ጊዜ ማቅረብ ተችሏል ነው ያሉት።
በሰሞነኛ ዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ችግር አባባሽ ግለሰቦችና ኩባንያዎች መኖራቸውን አንስተው፤ በቀጣይ ከነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ጋር ህግና ቴክኖሎጂን የተከተለ አሰራር እንደሚዘረጋ ጠቁመዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ፤ በነዳጅ ንግድ ላይ የሚታየው ሌብነት ለመከላከል የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ተጠያቂነት እንዲሰፍን አሳስቧል።
በጌታሰው የሽዋስ