የሀገር ውስጥ ዜና

በምክክር ሂደቱ የትግራይ ክልል ተሳትፎ …

By Mikias Ayele

April 01, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከበርካታ ችግሮች በኋላ ከትግራይ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያከናውነውን የመጀመሪያ ዙር የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የሀገራዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ልየታ መድረክ በአዲስ አበባ አስጀምሯል።

የለውጡ መንግሥት የፖለቲካ ስነ-ምህዳሩን ለማስፋት ዴሞክራሲ እና የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ልምምድ በኢትዮጵያ እንዲኖር ከማድረግ በተጨማሪ የቆዩ ቁርሾዎችን ለማረቅ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ስራ ካስገባ ሰነባብቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ታሪክ የመጀመሪያ በሆነው የምክክር ኮሚሽን በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የክልል ባለድርሻ አካላት፣ የፌዴራል ባለድርሻ አካላት እና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ አሰባስቧል፡፡

ኢትዮጵያውያን እንዲነሱ ወይም እንዲስተካከሉ የሚፈልጓቸውን ሀሳቦች በተወካዮቻቸው በኩል ለኮሚሽኑ በማስረከብ ለነገዋ ኢትዮጵያ ሀሳብ ሲያዋጡ በትግራይ ክልል ግን ባለው የሰላምና ፀጥታ ችግር ምክንያት የአጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ሳይከናወን ቆይቷል፡፡

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ሕገ ወጡ የህወሃት ቡድን ለሀገራዊ ምክክሩ ቀናኢ ትብብር አለማሳየቱ እና ቡድኑ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ እና የሲቪክ ድርጅቶች በነፃነት ተንቀሳቅሰው አጀንዳቸውን ማስረከብ እንዳይችሉ ማድረጉ የክልሉ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ እንዳይቀርቡ ቀዳሚ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ከክልሉ ወረዳዎች እና ዞኖች አጀንዳዎችን በማሰባሰብ እና በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ የመጀመሪያ ዙር የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የሀገራዊ ጉባኤ ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ ከኮሚሽኑ ጋር በአዲስ አበባ አከናውኗል፡፡

በዛሬው ዕለት የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በክልሉ ያሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድምፆችን ማሰማት፣ ቀደም ሲል ለተፈፀሙ ጥፋቶች የተጠያቂነት ስርዓትን ለማበጀት እንዲሁም በወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ ባለቤትነትን ማጎልበት ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡

የትግራይ ክልል በምክክር ሂደቱ መሳተፉ የክልሉ ህዝቡ በነገዋ ኢትዮጵያ የራሱን አሻራ ከማሳረፍ ባለፈ በባህልም ሆነ በታሪክ የጠንካራ እሴቶች መገኛ የሆነው የትግራይ ህዝብ ካለበት የግጭት አዙሪት እንዲወጣ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል።

በተጨማሪም የክልሉ የምክክር ተሳትፎ የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት ከተቋጨ በኋላ የተፈጠሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ቀደም ሲል ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ ውስጥ በንግግር እና በምክክር የማይፈታ ጥያቄም ሆነ ችግር የለም ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በሚኪያስ አየለ