አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የመጣው መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲፈጠር በርካታ ስትራቴጂዎችና ሪፎርሞች በመቅረጽ በመተግበር ላይ ይገኛል።
ከእነዚህም ውስጥ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ተደራሽ ለማድረግ ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በስፋት ተሰርቷል።
በዚህም ዜጎች በድንገተኛ ሕመም ወቅት ለከፍተኛ ወጪ ሳይጋለጡ ጥራት ያለውን ሕክምና እንዲያገኙ ለማስቻል ታስቦ የተዘረጋ ሥርዓት በመሆኑ በአገልግሎቱ በመታቀፍ መክፈል የማይችሉ ዜጎች በመንግስት ድጎማ እየተሸፈለነላቸው ይገኛል።
ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተተገበረ ሲሆን÷ በ2017 በጀት ዓመት ከ63 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ በማድረግ ከዚህ ውስጥ የ19 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ዓመታዊ የአባልነት መዋጮ በመንግሥት የተሸፈነ ነው።
እንዲሁም በተመሳሳይ በጀት ዓመት ከ13 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ቤተሰቦች አባል በመሆን የጤና መድኅን አገልግሎት ሽፋን ተጠቃሚ ተደርገዋል።
ኢትዮጵያ ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎትን የጀመረችበት ጊዜ አጭር ቢሆንም በዘርፉ እየተመተዘገበ የሚገኘው ዕድገት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ ጋር ሲነፃፀር የሚበረታታና በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን እንዲታቀፉ ማድረግ ያስቻለ ነው።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን ጉዞን ለማሳለጥ በተጀመረው አሰራር አገልግሎቱን ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር የተሳለጠ እንዲሆን የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
ይህም የኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት የፋይናንስ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥና አሰራሩን ለማዘመን እያከናወናቸው ካሉ መጠነ ሰፊ ስራዎች መካከል ዋነኛው ሆኖ ተጠቅሷል።
አገልግሎቱን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ በማዋል የወረቀት አልባ አገልግሎትን ለመስጠት በርካታ ስራዎች እየተከናወነ ይገኛል።
በዮናስ ጌትነት