አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ልማት ትብብራቸውን ለማጠናከር መክረዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በሀገራቱ መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ከቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ ምክትል ሊቀመንበር ሊዩ ዩንፌንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ የኢትዮጵያን የልማት ቅድሚያዎች በመደገፍ የሁለትዮሽ ትብብርን ማሳደግ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የልማት አጀንዳዎች በተመለከተ ገለጻ አድርገው፤ የሀገራቱ ትብብር መጠናከር ዘላቂ እድገትና መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
ሊዩ ዩንፌንግ በበኩላቸው ቻይና በፋይናንስ፣ በቴክኒክ እና በአቅም ግንባታ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ሁለቱም ወገኖች በባቡር መሠረተ ልማት፣ በግብርና፣ በዲጂታል ልማት፣ በኢንዱስትሪ እና በጤና ዘርፎች ላይ ትብብራቸውን ለማስፋት ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው ነው የተገለጸው፡፡
በሀገራቱ መካከል ያለውን አጋርነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተቋማዊ ትስስርን ለማጠናከርም ተስማምተዋል፡፡