የሀገር ውስጥ ዜና

በጠመንጃ ሳይሆን በሀሳብ ልዕልና የስልጣን ሽግግር የተደረገበት መጋቢት 24…

By Mikias Ayele

April 02, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መጋቢት 24 በጠመንጃ ሳይሆን በሀሳብ ልዕልና የስልጣን ሽግግር የተደረገበት እለት ነው አሉ የብልፅግና ፓርቲ ኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ነመራ ቡሊ፡፡

በጅማ ከተማ በሀገራዊ ለውጡ ለተገኘው ስኬት እውቅና የሚሰጥ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

አቶ ነመራ ቡሊ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የዴሞክራሲ ተምሳሌት እንድትሆን ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡

መጋቢት 24 ኢትዮጵያ በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሀሳብ ልዕልና የስልጣን ሽግግር ያደረገችበት እለት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የጅማ ዞን አስተዳደሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው፥ ከስምንት  አመት በፊት የመጣው ለውጥ ኢትዮጵያን ከብዙ ችግሮች የታደገና ታሪኳን በበጎ የቀየረ መሆኑን ተናግረዋል።

መጋቢት 24 የአፍሪካን ተስፋና የመደመር እሳቤን ያዋለደ ታሪካዊ ቀን ነው ያሉት ዋና አስተዳደሪው፥ ለውጡን በአንድነት መጠበቅና ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉት የጅማ ከተማና የዞኑ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ያለምንም ደም መፋሰስ ስርዓትን በማሻሻል የመጣው ለውጥ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የተመዘገበበት ነው ብለዋል፡፡

የመጋቢት 24 ፍሬዎችን በሁሉም ዘርፍ ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡

በወርቅአፈራው ያለው