አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ለውጡ ለሕዝቡ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ ነው አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ።
ርዕሰ መስተዳደሩ ሀገራዊ ለውጡ ዕውን የሆነበትን 8ኛ ዓመት አስመልክቶ በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሕዝባችን ታሪክ የግፍ ብቻ ሳይሆን የመራራ ትግልና የድል ታሪክ ጭምር ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ሕዝብ ለጭቆና ተንበርክኮ እንደማያውቅ አስታውሰው፤ በከፈለው መስዋዕትነት የማንነት፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥያቄዎቹን ደረጃ በደረጃ ሲያስመልስ መቆየቱን ገልጸዋል።
መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም እውን የሆነው ሀገራዊ ለውጥ ለሕዝቡ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ በመስጠት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን እየመለሰ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ሀገራዊ ለውጡ ተዳፍኖ የነበረው የባሕር በር ጥያቄ አጀንዳ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ይህንን ዕድል ለመጠቀም ስልታዊ አመራር በመገንባት ለትውልድ የሚተርፍ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም እያደረገ ስላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ግቦች መሳካት ሕዝቡ ዛሬም በከፍተኛ መስዋዕትነት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የብልጽግና ጉዞው ረጅም ቢሆንም ጅምሩ በትክክለኛ መንገድ ላይ እንደሚገኝም አጽንዖት ሰጥተዋል።