አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን ወደ ድንጋይ ዘመን እንመልሳለን ሲሉ፤ የኢራን ጦር በበኩሉ አንድም የጠላት ወታደር ከኢራን ምድር በህይወት አይወጣም ሲል አስጠነቀቀ፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢራን ጉዳይ ባደረጉት ንግግር፥ ጦራቸው በቀጣይ ሁለትና ሦስት ሳምንታት ውስጥ ከእስካሁኑ ጠንከር ያለ ጥቃት እንደሚፈጽም ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ በጦርነቱ የያዘችውን ግቦች ለማሳካት መቃረቧን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፥ ነገር ግን የኢራን ባለስልጣናት ያቀረብነውን የድርድር ሃሳብ ካልተቀበሉ ጦርነቱ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
የኢራን ጦር ጠቅላይ ሜጀር ጄነራል አሚር ሀታሚ በበኩላቸው፥ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የእግረኛ ጦር ዘመቻ ከጀመሩ አንድም የጠላት ወታደር ከኢራን ምድር በህይወት አይወጣም ብለዋል፡፡
ቴህራን ባለፉት ቀናት በቀጣናው ለአሜሪካ እና እስራኤል ይወግናሉ ባለቻቸው ሀገራት የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማቶች ላይ የፈጸመቻቸው ጥቃቶች ማስጠንቀቂያ መሆናቸውን ገልጻለች፡፡
የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማቶች ላይ መሰል ጥቃቶች የሚፈጸሙ ከሆነ ከዚህ የከፋ የአጸፋ ርምጃዎችን እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት መግለጫዎች ከአንድ ወር የተሻገረው የኢራን እና አሜሪካ-እስራኤል ጦርነት ከመቋጨት ይልቅ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል አመላካች መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡