ፋና ስብስብ

በለውጡ መንግሥት በባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡ ሥኬቶች…

By Melaku Gedif

April 03, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በለውጡ መንግሥት የብዝሃ ባህል ሃብቶች እና ሀገር በቀል እውቀቶችን በማልማት የሕዝቦችን ማህበራዊ ትስስር ማጠናከር ተችሏል አለ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፡፡

ሚኒስቴሩ በለውጡ መንግሥት ባለፉት ዓመታት በባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

የማብራሪያው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

1. የባህልና የቋንቋ ፖሊሲ ተፈጻሚነት፣

ረቂቅ ብሔራዊ የሀገር በቀል እውቀቶች ልማት ስትራቴጂ ተነድፏል፣ የህዝብ በዓላት አከባበር ለመወሰን በወጣው አዋጅ 1116/2017 መሰረት የህዝብ በዓላት አከባበር መመሪያ ተዘጋጅቷል፣ ረቂቅ የኢትዮጵያ ቋንቋ ፖሊሲ ፍኖተ ካርታ በመንደፍ እንዲሁም የሥነ ቃል ጥናትና ስነዳ ስትራቴጂ ረቂቅ ስነድ ተዘጋጅቷል፡፡

2. የብዝሃ ባህል ሀብቶችና ሀገር በቀል እውቀቶችን በማልማት የህዝቦች ማህበራዊ ትስስርን ከማጠናከር አንጻር፣

ከ100 በላይ ሀገር በቀል እውቀቶች በ10 የሀገር በቀል እውቀት ዘርፎች ምዝገባ ሲደረግ ባህሎችና ሀገር በቀል እውቀቶችን ለብሔሮች ብሔረሰቦች አብሮነት እና ለቀጣናዊ ትስስርና ገፅታ ግንባታ እንዲውሉ ተደርጓል።

የሀገር እድገትንና አንድነትን የሚያጎዱ ጎታች አመለካከቶችና ልማዶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ጥናቶችና ሀገራዊ ንቅናቄዎች ተደርገዋል፡፡ ባህልን ለብሄራዊ የጋራ ትርክት ግንባታ ለማዋል የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል በህዝቦች መካከል የጋራ ባህል እሴቶች ዳብረዋል (ብዝሃነትን መቀበል፤ሀገራዊ ብሄርተኝነትና የሃገር ፍቅር ስሜት መዳበር፤አብሮነት እና አንድነት እንዲጎለብት አድርጓል፡፡

በሁሉም ክልሎች የሀገር በቀል እውቀቶች ከማህበራዊ ፋይዳቸው በተጨማሪ በዕደ ጥበብ፣ ባህላዊ ምግብ እና መጠጥ፣ ባህል ህክምና የገቢ ማመንጫ ዘርፍ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡ በሀገራችን የሚገኙ 79 ሀገር በቀል የባህላዊ ፍትህና ዳኝነት ሥርዓቶች ፕሮፋይል ተሰንዷል። የባህላዊ ፍትህና ዳኝነት ስርዓቶች እንደ አማራጭ የፍትህ ሥርዓት ሆነው እንዲያገለግሉ ተደርጓል።

3. ከባህል ልማት አንፃር ባህላዊ የእርቅና ዳኝነት ሥርዓቶች ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎች /አፊኒ፣ ሄራ፣ የኔሞ ስርአት ሥራዎች ሲከናወኑ በዓላትንና ክብረበዓላትን በማልማት በሀገራችን የሚገኙ 83 ክበረ በዓላት ፕሮፋይል የማዘጋጀት፣ ክብረ በዓላት ለባህል መዳረሻነት እንዲውሉ ለማድረግ በ5 በዓላት ላይ ሰፊ የጥናትና ምርምር ስራዎች በመስራት ክብረ በዓላትን ለህዝቦች ማህበራዊ ትስስር ማዋል ተችላል፡፡

የብዝሃ ባህል ልማትን በማሳደግ የባህል ተቋማት ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃው እንዲጠናከሩ ተደርጓል፡፡ 87 የባህል ማዕከላትና መሰረተ ልማቶች ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

4. የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎችን በማልማት፣ ተጠቃሚነትና ተደራሽነቱን በማሳደግ የብዝሃ ቋንቋ ልማትን ማጎልበት ተችሏል፡፡ ቋንቋዎችን ዲጂታይዝ በማድረግ የብዝኃ ቋንቋ መማሪያ የአሰራር ፕላት ፎርም ማዘጋጀት፤ ለትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያ ባለሙያዎች የሞያ ብቃት ማረጋገጫ፣ ደረጃ ምደባ እና የስራ ፍቃድ በመስጠት አጠቃላይ አግልግሎት ማሳለጥ ተችላል፡፡

የትርጉም ሙያ ፍቃድ አሰጣጥ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ የአሪ፣ ኦንገታ ቋንቋ እና ባጫ፣ የኮሞ እንዲሁም የጠምባሮ ብሄረሰብ ቋንቋዎች መሰረተዊ የቋንቋ ስነዳ ስራዎች (ሰዋስው፣የመዝገበ-ቃላት የስነቃል) ተሰርቷል፡፡ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ልማት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ በትግባራ ላይ ይገኛል፡፡

አምስቱን የፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች ጨምሮ 30 የሚሆኑ ቋንቋዎች ዲጂታይዝ ተደርጓል፡፡ ቋንቋዎችን ዲጂታይዝ በማድረግ የብዝኃ ቋንቋ መማሪያ የአሰራር ፕላት ፎርም የተዘጋጀ ሲሆን÷ የሚዲያ ባለሞያዎችን የሚዲያ ቋንቋ አጠቃቀም ለማሻሻል ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዝኃን ባለስልጣንና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ስራ ተጀምሯል።