የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዘመናዊ የምርምር ማዕከልን ስራ አስጀመሩ

By Adimasu Aragawu

April 04, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በአርማወር ሐንሰን የምርምር ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባውን ዘመናዊ የምርምር ማዕከል መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

‎ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሳይንስ ሥነ ምሕዳር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከል ዛሬ መርቀን ከፍተናል ብለዋል።

ማዕከሉ ከመሠረተ ልማት ግንባታ ባለፈ ራሷን የቻለችና ጤናማ የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚተጋ የላቀ የዕውቀት ማዕከል እንደሆነ አመልክተዋል። ‎ የምርምር ማዕከሉ 40 ላቦራቶሪዎችን፣ የላቁ የጂኖሚክስ እና የባዮኢንፎርማቲክስ ቦታዎችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን ጥራትና ብቃት የሚያረጋግጥ የባዮኢኩዊቫለንስ ማዕከል ማካተቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለድንገተኛ አደጋዎች ዝግጁነትና ምላሽ የመስጠት አቅምን በመገንባት ረገድ እንደ ማገር ሆኖ ያገለግላልም ነው ያሉት።

‎ምርምርን ወደ ፖሊሲ፤ ፈጠራን ደግሞ ወደ ተግባራዊ መፍትሔ በመቀየር ይህ ማዕከል በመድኃኒት ምርት ራሳችንን ለመቻል፣ ዘላቂ የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ እስካሁን ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዳ ትልቅ ርምጃ ነው ሲሉም አብራርተዋል።