አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስቴር የ2018/19 የሰብል ምርት ልማት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ አስጀምሯል።
ሀገራዊ የሰብል ልማት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረኩ የክልሎች ግብርና ቢሮ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ በዚህ ወቅት፥ በተጀመረው ንቅናቄ መሠረት በየደረጃው ያሉ አካላት ለየት ያለ እቅድ በማዘጋጀት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የማዳበሪያ ሥርጭትና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ሥርጭት በአግባቡ ክፍተቶችን በማረም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ወደ ሥራ እንዲገቡ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
በመደመር መንግሥት እሳቤ መሠረት የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እስካሁን በዘርፉ ትልልቅ ውጤቶች ቢመዘገቡም ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አንፃር ዘርፉን አሁን ካለበት የበለጠ ወደላቀ ደረጃ የማሻገር ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት።
የግብርናውን ዘርፍ ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የከርሰ ምድር፣ የገፀ ምድር እና የዝናብ ውሀ ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በለውጡ መንግሥት የተጀመረውን በዓመት ሦስት ጊዜ የማምረት ሒደት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህ አካሄድ የኢትዮጵያ በምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የመደመር መንግሥት ያስቀመጠውን ግብ የማሳካት በየደረጃው ያሉ የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ትልቅ አደራ አለብን ብለዋል።
ለዘንድሮው ምርት ዘመን በቂ የማዳበሪያ አቅርቦት መኖሩንና ቅድሚያ የሚሰጡትን በመለየት በቶሎ ለአርሶ አደሮች ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የግብርናው ዘርፍ በመካከለኛው ምስራቅና ሌሎች አካባቢዎች የተከሰቱ ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች ግንባር ቀደም ሰለባ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን በተፈጠረው የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ተከትሎ በቀጣይ ሊከሰት የሚችለውን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ በየደረጃው የሚገኙ አካላት አርሶ አደሮችን በማብቃት የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በስፋት የማምረት ሂደቱ በሁሉም አካባቢ ሊተገበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ተፅዕኖውን በመቋቋም በዘርፉ የተመዘገበውን ድል አሁን በመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየር ድል በዘርፉ የላቀ ድል ማስመዝገብ አለብን ብለዋል።
ግብርናውን የማዘመን ሒደት ለማስቀጠል የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች አቅርቦት ላይ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
በመሳፍንት ብርሌ