የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያን የማጽናት ጉዳይ ታስቦበት እየተከወነ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

April 04, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ችግሮችን ሁሉ ወደ ዕድል በመቀየር ኢትዮጵያን የማጽናት ጉዳይ ታስቦበት እየተከወነ ነው አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ ስፖርት ፓርክ መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ ካዛንችስ አካባቢ ከዚህ ቀደም በስፋት የተለመደው የጫት እና የሺሻ ቦታ መበራከት ነው፤ አሁን ግን በብዙ መልኩ አብባለች አምራለች፤ ይሄንንም ስፍራ ይዛለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ታዳጊዎች የሚሰሩበት፣ የሚያድጉበት፣ የሚወዳደሩበት እና የሚልቁበት አውድ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

በጣም ተስፋ ሰጪ ሥራዎች አሉ፤ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እየተሰራች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ችግሮችን ሁሉ ወደ ዕድል በመቀየር ኢትዮጵያን የማጽናት፣ የመሥራት እና የማቆም ጉዳይ ታስቦበት እየተከወነ ነው ብለዋል።

የተጀመሩ ስራዎች ሁሉ አምረውና አብበው እያለቁ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ትውልድ ይህንን የሥራ፣ የመነሳት እና የመንቃት ዘመን አድርጎ የሚያወሳበት ጊዜ ይመጣል ነው ያሉት።

የጀመርነውን፣ ያሰብነውን ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት የምንፈልገውን ልጆቻችን እንዲያዩና እንዲኖሩበት እየሰራን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ትብብር፣ መደማመጥ፣ ማስተዋልና በሙሉ ልቦና አርቆ ማየት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የአዲስ ስፖርት ፓርክ ፕሮጀክት ተሰርቶ እስኪጠናቀቅ ከተማ አስተዳደሩን ጨምሮ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ያበረከቱ አካላት በማመስገን የአዲስ አበባ ታዳጊዎችና ወጣቶች ወደዚህ ቦታ በመምጣት ጊዜ እንዲያሳልፉ፣ ራሳቸውን እንዲሰሩ፣ አካላቸውን እንዲያበለጽጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በዮናስ ጌትነት