አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጣቶች የፈጠራ ብቃታቸውን እንዲያወጡ በማድረግ ረገድ ሰፊ ስራ ይጠበቅባቸዋል አሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እና በስታርት አፕ ፖሊሲ አዋጅ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት አካሂዷል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በሀገር አቀፍ ደረጃ የቴሌኮም ዘርፉን ጨምሮ በዲጂታል ግብይትና አሰራር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል።
በዚህም በሁለት የቴሌኮም አቅራቢ ተቋማት በርካታ የሕበረተሰብ ክፍሎች የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ 70 ሚሊየን ሰዎች ተጠቃሚ ማድረጉን አንስተዋል።
በኢንተርኔት ደረጃ 56 ሚሊየን ሰው ተጠቃሚ መሆኑና ይህም ዲጂታል ግብይትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት በዲጂታል መንገዶች እንዲከወኑ እድል ፈጥሯል ብለዋል።
አሁን ላይ ሀገሪቱ ዲጂታል 2030ን እያሳለጠች እንደምትገኝ ገልጸው÷ ወቅቱ የደረሰበትን ሰው ሰራሽ አሰተውሎትን ጨምሮ ቴክኖሎጂውን በግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት እና ሌሎች ዘርፎች የበለጠ ለመጠቀምና ለልማት አጋዥ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እቅድና በተለይም ወጣቶች የበለጠ የፈጠራ ብቃታቸውን እንዲያወጡ በማድረግ ረገድ ሰፊ ስራ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ ዘርፍ በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸው÷ ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በከድር መሀመድ