አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍኤምሲ) ሰራዊቱ ሀገርን ከመጠበቅ ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሂደት አሻራውን እያሳረፈ ይገኛል አለ በመከላከያ ሰራዊት የግብርና ልማት ዘርፍ፡፡
መከላከያ ሰራዊት በግብርና ዘርፍ ያከናወናቸውን የልማት ተግባራት በ2018/19 የምርት ዘመን ሀገር አቀፍ የሰብል ልማት ንቅናቄ ላይ አቅርቧል፡፡
በተቋሙ የግብርና ልማት ዘርፍ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀኔራል እሸቴ አራጌ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ ሰራዊቱ ሀገርን ከመጠበቅ ጎን ለጎን በግብርና ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
መከላከያ ሰራዊት የህዝቡ አብራክ ክፋይ እንደመሆኑ አርሶ አደሩን በተለያየ መንገድ ለረዥም ጊዜ ሲደግፍ ቆይቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሰራዊቱ የሀገር ሉዓላዊነት አስከባሪ ብቻ ሳይሆን ገበሬም ጭምር መሆኑን አውስተው፥ የምግብ ሉዓላዊነትን እውን ለማድረግ የተጀመረውን ብሔራዊ ግብ ለማገዝ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
የመከላከያ ግብርና ተቋም በቅርብ ጊዜ የተቋቋመ ቢሆንም የግብርና ሚኒስቴር ባስቀመጣቸው ግቦች መሰረት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሰራዊቱ በተለያዩ አካባቢዎች የግብርና ልማት ማዕከላትን በማዘጋጀት ሰብሎችን፣ ፍራፍሬዎችና ተክሎችን በማልማት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የሀገር ሰላምንና የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ተግባር ለአንድ አካል ብቻ የተተወ ኃላፊነት ሳይሆን የሁሉም የጋራ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
ግብርና ሚኒስቴር እና ክልሎች ለተቋሙ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በቀጣይም በየደረጃው ያለው የፖለቲካ አመራር ሰራዊቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት እንዲደግፍ ጠይቀዋል፡፡
በመሳፍንት ብርሌ