አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ ከፍተኛ ባለስልጣንን ለመግደል ባደረገው ሙከራ ቡድኑን የሚቃወሙ ሌላ ባለስልጣን በስህተት ተገደሉ፡፡
በጥቃቱ የተገደሉት ፒየር ሙዋድ የተባሉት የሊባኖስ ባለስልጣን በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሰውን ሄዝቦላህ በጽኑ ይቃወሙ እንደነበር ነው የተገለጸው፡፡
የእስራኤል ጦር በሊባኖስ የሚገኝን የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራር ለመግደል ባደረገው ሙከራ የታቀደውን ኢላማ መምታት አለመቻሉን በመጥቀስ በክስተቱ ማዘኑን ገልጿል፡፡
በግለሰቦች መኖሪያ ቤት ላይ በተፈፀመው ጥቃት ከተገደሉት የሊባኖሱ ከፍተኛ ባለስልጣን እና ባለቤታቸው በተጨማሪ በሌሎች ንጹሃን ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በምስራቃዊ ቤይሩት በምትገኘው ኤይን ሳዴህ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት በአጠቃላይ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል፡፡
የሊባኖስ ኃይሎች ፓርቲ በበኩሉ፥ በጥቃቱ የተገደሉት ፒየር ሙዋድ ወታደራዊ አባል ያልነበሩ ሲቪል ሰው መሆናቸውን በመጠቅስ ባለስልጣኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የፋሲካ በዓልን እያከበሩ ነበር ብሏል፡፡
የሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር በሚያደርገው ጦርነት በንፁሃን ዜጎች ላይ በርካታ ጉዳቶችን እያደረሰ መሆኑን የገለጸው ፓርቲው፥ የቡድኑን እንቅስቃሴ አውግዟል፡፡
በሚኪያስ አየለ