ዓለምአቀፋዊ ዜና

እስራኤል በኢራን ቁልፍ የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ጥቃት ፈፀመች

By sosina alemayehu

April 06, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍኤምሲ) የእስራኤል ወታደራዊ ሀይል በኢራን ቁልፍ የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ጥቃት ፈፅሜያለሁ አለ፡፡

ጥቃቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰጡት ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ሰዓታት ብቻ በቀሩበት ጊዜ እና ፕሬዚዳንቱ በኢራን የሀይል መሰረተ ልማት ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም ከዛቱ በኋላ የተፈጸመ ነው ተብሏል፡፡

ጥቃት የተፈፀመበት የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ አሳሉያህ በተባለ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ግማሽ ያህሉን የኢራን የኬሚካል ምርት ያመርት ነበር ተብሏል፡፡

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ያለውን አቅም በሙሉ ተጠቅሞ የኢራን መሰረተ ልማቶች ላይ ርምጃ ይፈጽማል።

በፔትሮኬሚካል ፋብሪካው ላይ የተፈጸመው ጥቃትም የዚሁ ርምጃ አካል መሆኑን መጥቀሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ኢራን በበኩሏ እስራኤል ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ በዛሬው ዕለት ቀርቦ የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳብ ውድቅ ማድረጓን ገልጻለች።

ኢራን ፍላጎቷ ተኩስ ማቆም ሳይሆን ዳግም ጥቃት እንደማይፈጸምባት ዋስትና በማግኘት ጦርነቱ የሚቋጭበት ሁኔታ እንዲፈጠር መሆኑን መግለጿን የሞርኒንግ ስታር ዘገባ አመልክቷል።

‘ኦፕሬሽን ኢፒክ ፊዩሪ’ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በአሜሪካ እና እስራኤል ጥምረት እየተካሄደ ያለው ዘመቻ እንዲሁም የኢራን አጸፋ እንደቀጠለ ሲሆን፤ በዛሬው እለት የእስራኤል ጦር የኢራን አብዮታዊ ዘብ የደህንነት ሹም ሜጀር ጀኔራል መጂድ ኻደሚ ላይ ግድያ መፈጸሙ ይታወቃል።

በሚኪያስ አየለ