የሀገር ውስጥ ዜና

በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት የተገነቡ የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካዎች በግብአት ራሳቸውን እንዲችሉ እየተሰራ ነው

By sosina alemayehu

April 06, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍኤምሲ) የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ጽ/ቤት በጽ/ቤቱ የተገነቡ የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካዎች በግብአት ራሳቸውን እንዲችሉ እየተሰራ ነው አለ።

ጽ/ቤቱ በቀን 300 ሺህ ዳቦ እና 420 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም ያላቸው 14 የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካዎችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ገንብቷል።

ዘላቂ ልማትን ለማምጣት መሰረት በማድረግ በጽ/ቤቱ እየተተገበሩ ካሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካዎችን ገንብቶ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ አንዱ መሆኑን ገልጿል።

የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካዎቹ በአነስተኛ ዋጋ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን አስረድቷል።

ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው በአነስተኛ ዋጋ ለህብረተሰቡ ምርታቸውን ማቅረብ የሚችሉበትን ስልቶች በመንደፍ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም አመላክቷል።

በዚህ መሰረት ፋብሪካዎቹ የሚገኙባቸው አካባቢዎች ለስንዴ ምርት የሚሆን እርሻ መሬት በማዘጋጀት፣ በግብአት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሷል።

በአፋር ክልል ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኘው የሰመራ ብርሀን ዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካ 500 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ገልጾ፤ በመጀመሪያው ዙር 100 ሄክታር መሬት የተዘራ ስንዴ ምርት ተሰብስቧል ብሏል።

ከዚህም 2 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት ለማምረት መቻሉን ጽ/ቤቱ ባወጣው በመረጃው ጠቁሟል።