ስፓርት

ሪያል ማድሪድ ከባየርን ሙኒክ

By Adimasu Aragawu

April 07, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ዛሬ ምሽት ሪያል ማድሪድ ከባየርን ሙኒክ የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡

የ15 ጊዜ የመድረኩ ባለክብር ሪያል ማድሪድን ከ6 ጊዜ የመድረኩ አሸናፊ ባየርን ሙኒክ ጋር የሚያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ከወዲሁ ትኩረት አግኝቷል፡፡

ሪያል ማድሪድ በ16ቱ ጥሎ ማለፍ የእንግሊዙን ክለብ ማንቼስተር ሲቲን በድምር ውጤት 5 ለ 1 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡

ተጋጣሚው ባየርን ሙኒክ በበኩሉ የጣሊያኑን ክለብ አታላንታ በድምር ውጤት 10 ለ 2 በመርታት ለሩብ ፍጻሜው መብቃቱ የሚታወስ ነው፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ ሁለቱን ሲያሸንፍ ባየርን ሙኒክ በአንዱ ድል አድርጎ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡

በሁሉም ውድድሮች ከአምስት ተከታታይ ድል በኋላ በሳምንቱ መጨረሻ በማዮርካ የተሸነፈው ሪያል ማድሪድ ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

የቡንደስሊጋው መሪ ባየርን ሙኒክ በአንጻሩ በሁሉም ውድድሮች ለ12 ጨዋታዎች የዘለቀውን ያለመሸነፍ ጉዞ ለማስቀጠል ከባድ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ባቫሪያኑ በዚህ የውድድር ዓመት አስፈሪ የፊት መስመር ተጫዋች ካላቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን፥ ሀሪ ኬን፣ ሉዊስ ዲያዝ፣ ኦሊሴ እና ሰርጅ ናብሪ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በቪንሰንት ኮምፓኒ የሚመራው ባየርን ሙኒክ በዚህ የውድድር ዓመት በቡንደስሊጋው ብቻ 100 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

በመከላከሉ ረገድ ችግር ለሚነሳበት ለስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ የባየርን ሙኒክ የፊት መስመር ተጫዋቾች ፈታኝ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

ያለ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂው ቲቦ ኮርቱዋ ወደ ሜዳ የሚገባው ሪያል ማድሪድ በጨዋታው በተለይም የፌዴሪኮ ቫልቬርዴ፣ ቪኒሸስ ጁኒየር፣ ጁድ ቤሊንግሀም እና ኪሊያን ምባፔን ምርጥ ብቃት ይፈልጋል፡፡

ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሳንቲያጎ ቤርናባው ስታዲየም የሚደረገውን ተጠባቂ ጨዋታ እንግሊዛዊው ዳኛ ማይክል ኦሊቨር በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት አርሰናል ወደ ፖርቹጋል ተጉዞ ስፖርቲንግ ሊዝበንን ይገጥማል፡፡

በሳምንቱ መጨረሻ ከኤፍ ኤ ዋንጫ የተሰናበተው አርሰናል በቀሩት ሁለት ውድድሮች ላይ የሚያደርገው ጉዞ ይጠበቃል፡፡

ከ15 ቀናት በፊት ለአራትዮሽ ዋንጫ ሲፎካከር የቆየውና ከሁለቱ ዋንጫዎች ውጪ የሆነው አርሰናል አሁን የሚቀሩት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድሮች ብቻ ናቸው፡፡

አርሰናል በ16ቱ ጥሎ ማለፍ ባየር ሊቨርኩሰንን በድምር ውጤት 3 ለ 1 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ሲቀላቀል፥ ተጋጣሚው ስፖርቲንግ ሊዝበን በበኩሉ ቦዶ ግሊምትን 5 ለ 3 በመርታት ለሩብ ፍጻሜው መብቃቱ ይታወሳል፡፡

ስዊድናዊው የአርሰናል የፊት መስመር ተጫዋች ቪክተር ዮኬሬሽ የቀድሞ ቡድኑን በተቃራኒ የሚገጥም ይሆናል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ