አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አንጋፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አምባሳደር ቆንጂት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በ1950ዎቹ በለጋ እድሜያቸው ተቀላቅለው ከዴስክ ኦፊሰርነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት አገልግለዋል።
አምባሳደር ቆንጂት ከዮዲት እምሩ በመቀጠል በኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደርም ናቸው።
አምባሳደሯ በኦቶዋ፣ ካይሮ፣ ቴል አቪቭና ቬይና በሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን÷ በአፍሪካ ሕብረትና በተባባሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ መልዕክተኛ በመሆንም ሰርተዋል።
ከሰኔ 2009 እስከ መስከረም 2011 ዓ.ም ደግሞ ኢጋድ በመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ላይ ልዩ አማካሪ ሆነው ማገልገላቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
ሚኒስቴሩ በአምባሳደር ቆንጂት ሕልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ለሟች ቤተሰቦች እና ወዳጆች መጽናናትን ተመኝቷል።