ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኢራን የቀረበላትን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሃሳብ ውድቅ አደረገች

By Hailemaryam Tegegn

April 07, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር የገባችበትን ጦርነት ለማስቆም የቀረበውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሃሳብ ውድቅ አደረገች፡፡

በፓኪስታን አደራዳሪነት እየተካሄደ በሚገኘው የሰላም ጥረት የቀረበው ምክረ ሃሳብ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግና በ20 ቀናት ውስጥ ዘላቂ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የሚጠይቅ ነው፡፡

ቴህራን በበኩሏ በአሜሪካ የቀረበውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሃሳብ ውድቅ በማድረግ ግጭቱን ለመፍታት መፍትሄ ያለቻቸውን 10 ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጣለች፡፡

ኢራን ካስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የተጣሉባት ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች እንዲነሱ፣ እስራኤል በሄዝቦላ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት እንድታቆም የሚሉት ይገኛሉ፡፡

በምላሹ ቴህራን የሆርሙዝ ሰርጥን በመክፈት ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ እንዲሰፍን እንደምታደርግ ገልጻለች፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን የማትከፍት ከሆነ በሀገሪቱ የኃይል ማመንጫዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ አስጠንቅቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለኢራን የቀረበው የተኩስ አቁም ሃሳብ በጣም ጠቃሚ እርምጃ ነው ያሉ ሲሆን፥ ግጭቱን ለማስቆም ግን በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ኢራን ጦርነቱን በዘላቂነት ማቆም ብቻ ተቀባይነት እንዳለው በመግለጽ ሃሳቡን ውድቅ ማድረጓን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ