አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለውን የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር አዋጅን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል።
የምክር ቤቱን 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤን እና የተሻሻለውን የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን በሚመለከት ከግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርትና ውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ነው ምክር ቤቱ ያጸደቀው።
በሕዝብ ምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ ሪፖርቱንና የውሳኔ ሃሳቡን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ለግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች።
የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋት፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አዋጅ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
አዋጁ በዚህ ረገድ የግብርና ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅና ጥቅም ላይ ማዋል እንዲሁም የግብርና ቢዝነስን ለማስፋት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅን እና የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መምራቱን የዘገበው ኢዜአ ነው።