አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለአቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር አከናውነዋል።
የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት እንደሀገር ከሚያከናውናቸው ማህበረሰብ ተኮር ስራዎች ጎን ለጎን በበዓላት ወቅት ማዕድ የማጋራት ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል፡፡
በዚህም መሰረት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለመጪው የትንሳኤ በዓል በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ለሚገኙ 150 የማህበረሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋርተዋል።
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በዚሁ ወቅት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ጽህፈት ቤታቸው ማህበረሰብ ተኮር ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በማዕድ ማጋራት መርሐ ግብሩ የዱቄት እና ዘይት ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፥ የዱቄት ምርቱ ጽ/ቤቱ ያስገነባቸውና ለሕብረተሰቡ በዝቅተኛ ዋጋ ግልጋሎት እየሰጡ ከሚገኙ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካዎች የተገኘ ነው።
ዘላቂ ልማትን መሰረት በማድረግ በጽ/ቤቱ እየተተገበሩ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የዳቦና ዱቄት ፋብሪካዎችን ገንብቶ ለህብረተሰቡ ማቅረብ መሆኑ ይታወቃል፡፡