የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ህብረት በአምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገለፀ

By Mikias Ayele

April 07, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት በአንጋፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡

ህብረቱ ባወጣው የሀዘን መግለጫ አምባሳደር ቆንጂት በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ፈር ቀዳጅ የነበሩና ህይወታቸውን ከሀገር ባለፈ ለአህገሪቱ በማገልገል ያሳለፉ ፓን አፍሪካዊ እንስት ነበሩ ብሏል፡፡

በርካታ አስርት ዓመታትን በውጭ ጉዳይና ዲፕሎማሲ ስራ ማሳለፋቸውን የገለጸው ህብረቱ፥ ይህ ተግባራቸው ለአፍሪካ ሴት ዲፕሎማቶች መንገድ የከፈተ ነው ብሏል፡፡

አምባሳደሯ በኃላፊነት ዘመናቸው የአፍሪካን ጥቅም ለማስጠበቅና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሶ፥ በአፍሪካ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የጋራ አጀንዳዎች በማሰተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን አውስቷል፡፡

የአምባሳደሯ ህያው ስራ የአፍሪካ ሴት ዲፕሎማቶች በድፍረት እና በዓላማ እንዲያገለግሉ ዓርዓያ ሆኖ ይቀጥላል ብሏል፡፡

ህብረቱ በመልዕክቱ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለኢትዮጵያ መንግስትና ለመላው አፍሪካዊ ወዳጆቻቸው መፅናናትን ተመኝቷል፡፡