አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማሕበረሰብ አቀፍና መረጃ መር የወንጀል መከላከልን በማስፋት ከሀገር አልፎ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል እየተሰራ ነው አሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፡፡
“ፖሊሳዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሐሳብ 20ኛው የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።
ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተከናወነው የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም የፖሊስ ኃይል ሀገራዊ ተልዕኮዎችን በብቃት በሚወጣበት ቁመና ላይ እንዲገኝ ማድረግ ተችሏል፡፡
ዘመናዊ ትጥቅ እና ሎጂስቲክስ ማሟላትን ጨምሮ ጊዜውን የሚመጥን የሰለጠነና ፕሮፌሽናል የፖሊስ ኃይል ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በውጭ እና በሀገር ውስጥ አጋርነቶችንና ቅንጅቶችን በማስፋት የወንጀል መከላከልና የወንጀል ምርመራ አቅም ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ጠንካራ የፖሊስ ተቋም በመገንባት እና በፌደራል ፖሊስ የተፈጠረውን አቅም ወደ ክልል ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በጉባኤው የኢትዮጵያ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታን ለማስጠበቅ ከፖሊስ ኃይል የሚጠበቁ ተግባራትን በተመለከተ ሰፊ ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በለይኩን ዓለም