አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ የመጨረሻው የአምስት ዓመት የማስፋት ምዕራፍ የትግበራ ማስፈፀሚያ እቅድን አጽድቀናል አሉ፡፡
የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን፣ ስርዓተ ምግብና ሰቆጣ ቃል ኪዳን፣ የጤና መድህን፣ የጽዱ ኢትዮጵያ የማስፋፊያ አድቮኬሲና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀምን በተመለከተ በበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የምግብና ስርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እድገት መሳካት የጀርባ አጥንት ለሆነው አምራችና ተመራማሪ ሀይል ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።
በፌዴራል ደረጃ የተከለሰው የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ መጽቀዱን ገልጸው፥ በፍኖተ ካርታው የታቀዱ ቁልፍ የትራንስፎርሜሽን ተግባራት በተጠሪ መስሪያ ቤቶችና ክልል ቢሮዎች ተካትተው እንዲተገበሩም አቅጣጫ አስቀምጠናል ነው ያሉት።
በተመሳሳይ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ያሉ ሲሆን፥ በቃል ኪዳኑ የ15 ዓመት ፍኖተ ካርታ መሰረት የመጨረሻው የአምስት ዓመት የማስፋት ምዕራፍ (2019 – 2023 ዓ.ም) የትግበራ ማስፈፀሚያ እቅድ መፅደቁን ገልጸዋል።
በዚህም የመቀንጨርንና ሌሎች የስርዓተ ምግብ ችግሮች ምጣኔን በፍጥነት ለመቀነስ የተገኙ ልምዶች በመቀመር፣ ማህበረሰቡን በባለቤትነት የማሳተፍ ስራን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም የፌዴራል የምግብ ስርዓትና ስርአተ ምግብ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይተን የባለድርሻ አካላት ግብአት ተካቶበት ወደ ቀጣይ አፈጻጸም እንዲሔድ አቅጣጫ አስቀምጠናል ነው ያሉት።
የጤና መድኅን ስራን በተመለከተ በክልል ደረጃ ጠንካራ አስፈጻሚ አካላትን በማደራጀት እንዲሁም በያዝነው ዓመት የፌደራል ቋት መመስረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መግባባት ላይ መደረሱንም አመልክተዋል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅንን በውጤታማነት ለማስቀጠል እንዲቻል የመክፈል አቅምን መሰረት ያደረገ የመዋጮ መጠን ትግበራን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የጤና መድህን ያለው ለሌለው የሚደጋገፍበትና የሚረዳዳበት ወሳኝ ፕሮግራም እንደመሆኑ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ማሳተፍና ማረባረብ እንደሚገባን ከስምምነት ደርሰናል ብለዋል፡፡
የጽዱ ኢትዮጵያ የማስፋፊያ አድቮኬሲና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ የ5 ዓመታት ትግበራን በተመለከተ ትግበራው በንቅናቄ እንዲመራ ማድረግ እንደሚገባ ከውሳኔ ላይ መደረሱንም አንስተዋል፡፡
በዚህም በፌደራልና በክልል ደረጃ ለፕሮግራሙ ትኩረት በመስጠት በቂ በጀት እንዲመደብ ማድረግና ከተለያዩ ምንጮች የሀብት ማሰባሰብ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀምጠናል ብለዋል፡፡