ዓለምአቀፋዊ ዜና

በኢስታንቡል የእስራኤል ቆንጽላ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሽብር ድርጊት ነው – ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን

By Hailemaryam Tegegn

April 07, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱርክ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ኢስታንቡል በሚገኘው የእስራኤል ቆንጽላ ጽ/ቤት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ጭካኔ የተሞላበት የሽብር ድርጊት ነው አሉ ፡፡

በዛሬው ዕለት ኢስታንቡል በሚገኘው የእስራኤል ቆንጽላ ጽ/ቤት ላይ የተቃጣ የሽብር ጥቃት ሙከራ መክሸፉን የቱርክ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ሙስጠፋ ቺፍትቺ ተናግረዋል፡፡

ፖሊስ ጥቃቱን ሊፈጽሙ በነበሩ ሦስት ግለሰቦች ላይ በወሰደው ርምጃ አንደኛው ሲገደል ሁለቱ ቆስለው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

ጥቃቱን ለማምከን በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሁለት የፖሊስ አባላት መጎዳታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በተኩስ ልውውጡ የተገደለው ግለሰብ በተለይም በቀጣናው ከሚንቀሳቀሰው የአይ ኤስ ሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

አሸባሪዎቹ ርምጃ ከተወሰደባቸው በኋላ በተደረገ ፍተሻ ዲጂታል የግንኙነት መሳሪያዎችን ይዘው መገኘታቸውንና በግለሰቦቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን ጥቃቱን ጭካኔ የተሞላበት የሽብር ድርጊት ሲሉ ያወገዙ ሲሆን፥ ሽብርተኝነትን መዋጋታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የእስራኤል ኤምባሲ በበኩሉ ድርጊቱን በማውገዝ በወቅቱ ሰራተኞቹ በጽ/ቤቱ ውስጥ አልነበሩም ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በሚኪያስ አየለ