ዓለምአቀፋዊ ዜና

ዓለምን ከጫና ያወጣው የተኩስ አቁም ስምምነት

By Adimasu Aragawu

April 08, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን እና አሜሪካ ያደረጉትን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ የተለያዩ የዓለም ሀገራት ደስታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

የዓለምን አኮኖሚ እና ፖለቲካ ጫና ውስጥ የከተተው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት 36 ቀናትን ተሻግሮ ምሽት ላይ በኢራን እና አሜሪካ መካከል ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምት ተደርጓል።

በስምምነቱ መሰረት ኢራን በመከላከያ ኃይሏ አጃቢነት የሆርሙዝ ወሽመጥን ክፍት እንደምታደርግ ተገልጿል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ መስማማታቸውን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ÷ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለውይይት እድል የሚሰጥ እና ዘላቂ የተኩስ አቁም ለማድረግ መንገድ የሚከፍት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ጃፓን፣ ኢራቅ፣ ግብፅ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያ፣ አውስትራሊያ፣ ኒውዚላንድ እና ሌሎች በርካታ ሀገራት በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤታቸው በኩል በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምት መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሀገራቱ ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ መጠየቃቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በአንድ በርሜል 13 በመቶ ገደማ በመቀነስ 94 ነጥብ 8 ዶላር እየተሸጠ መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በሚኪያስ አየለ