ቢዝነስ

በኦሮሚያ ክልል ለትንሳዔ በዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በበቂ ሁኔታ ለገበያ እየቀረቡ ነው

By Melaku Gedif

April 08, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለትንሳዔ በዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አለ የክልሉ ንግድ ቢሮ፡፡

በቢሮው የገበያ ልማት ዳይሬክተር ጉቱ ተመስገን እንዳሉት ÷ በበዓሉ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይከሰት ኮሚቴ ተዋቅሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ተሰርቷል፡፡

በዚህ መሰረትም ከመደበኛ ገበያ በተጨማሪ በባዛሮችና ኤግዝቢሽኖች እንዲሁም በቅዳሜና እሑድ ገበያዎች የበዓል ፍጆታ እቃዎች ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

ለበዓሉ የቁም እንስሳት፣ በጎች እና ፍየሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 600 ሺህ በላይ የእርድ እንስሳት ለገበያ እየቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

3 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ዶሮዎች እና በቂ እንቁላል ለበዓሉ በተለያዩ ገበያዎች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡

በተጨማሪም አትክልትና ፍራፍሬ፣ ዘይት፣ ስኳር እና ሌሎች የበዓል መሰረታዊ ፍጆታዎች ለሕብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ለትንሳዔ በዓል በቂ ምርት መኖሩን ተገንዝቦ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሸምት ያስገነዘቡት ዳይሬክተሩ÷ ነጋዴዎች አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ እንዲቆጠቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዜጎች ለበዓሉ ጊዜ ያለፈባቸውና ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸው ምርቶችን እንዳይገዙ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አቶ ጉቱ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በበዓል ገበያው ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ