የሀገር ውስጥ ዜና

ከንቲባ አዳነች የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ233 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ማዕድ አጋሩ

By Melaku Gedif

April 08, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ ከ233 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ማዕድ አጋርተዋል፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው የሀገር ባለውለታ አረጋውያንና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች ማዕድ አጋርተናል ብለዋል።

ይህ ተግባር በከተማዋ የማዕከል መስሪያ ቤቶች፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች እየተከናወነ ያለ በጎ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በሁሉም በዓላት የምናደርገው የማዕድ ማጋራት፣ ድጋፍ የሚሹ የከተማችን ነዋሪዎችን “ምን ጎደለ?” ብለን በመመልከትና በመጠየቅ ክፍተታቸውን የምንሞላበት፤ ለነዋሪዎቻችን ያለንን ክብር የገለፅንበት ሰው ተኮር ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ማዕድ ከማጋራት ባለፈ በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ግጭትና በነዳጅ እጥረት ሳቢያ የሚከሰተውን ጊዜያዊ የኑሮ ጫና ለማቃለልና የገበያ ጉድለትን ለመሙላት ከፍተኛ በጀት በመመደብ መሰረታዊ ምርቶች በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ እያደረግን እንገኛለን ነው ያሉት።

በዚህም የምርት እጥረት እንዳያጋጥም በተከናወነው ሥራ በመዲናዋ የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ እንዲሰፍን መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡

ወቅታዊ ችግሮችን ለመሻገር የሚከናወኑ እነዚህ ተግባራት በሙሉ ከለውጡ ወዲህ የጀመርነው የ”ሰው ተኮር” ሥራዎቻችን አካል ናቸው ብለዋል ከንቲባዋ።

አዲስ አበባ ለሁሉም እኩል የተመቸች ፣ ሥራዎች ማንንም ያልዘነጉ አካታች እንዲሆኑ እየተሰራ ሲሆን÷ ከተማዋ እየተቀየረችና እየተለወጠችበት ያለው ልማት በሰው ኑሮና አኗኗር ላይ ለውጥ እያመጣ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በሁሉም ክ/ከተሞችና ወረዳዎች ለሚደረገው ማዕድ ማጋራት ለተባበሩ ልበ ቀና ባለሃብቶች እንዲሁም ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻቸው ሁሌም እየተሸከሙ በጉልበታቸው በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገሉ ላሉ ወጣቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ለዛሬው ማዕድ ማጋራት ጆስፖንድ ትራዲንግ 15 ሚሊየን ብር፣ አቶ ጀማል አሕመድ (ሚድሮክ) 10 ሚሊየን ብር፣ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን 7 ሚሊየን ብር፣ አቶ በላይነህ ክንዴ (ቢኬጂ) 5 ሚሊየን ብር፣ አትሌት ዮሐንስ ቢፋ 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር እና አቶ ተካበ ሙሉ 500 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የትንሳኤ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን ፍቅሩን እስከ መስቀል የገለጸበትና በትንሳኤ የምስራች የተበሰረበት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አውስተዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር በታላቅ ፍቅር፣ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ያለንን መተሳሰብ በተግባር በመግለጽ፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም፣ የአብሮነት ምክንያት በመሆን ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡