አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የግልግል ዳኝነት መድረክ በበቂ ማስረጃ በመከላከል መርታት ችላለች አለ ፍትሕ ሚኒስቴር።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴዔታ በላይሁን ይርጋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ÷ አክጉን ማኪና ሳናይ ቪ ዲ ቲካሬት የተባለ ኩባንያ ከአዲስ አበባ የንጹህ ውሃ አቅርቦት ዋና ምንጮች ከሆኑት ለገዳዲና ድሬ ግድቦች አቅራቢያ እንዲያለማ ተሰጥቶት በነበረው ይዞታ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሕጉ በሚያዘው መሠረት እንዲያቀርብ በተደጋጋሚ ለቀረበለት ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጥ አለመቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት የኢንቨስትመንት ሥራውን ከግድቦቹ ራቅ ወዳሉ ቦታዎች እንዲያዛውርና የተጽዕኖ ግምገማ ሪፖርት እንዲያቀርብ የተነገረው መሆኑን እንዲሁም አማራጭ ምቹ ቦታዎች በተለዋጭነት ቀርበውለት እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡
የቀረበለትን አማራጭ ባለመቀበል የኢንቨስትመንት ጥበቃ መብት ጥስት ደርሶብኛል በሚል የ500 ሚሊየን ዶላር ካሳ ክስ ማቅረቡን እና ኢትዮጵያ በበቂ የክርክር አቅም መርታቷን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለዜጎቹ ከሚያቀርበው ንጹህ የመጠጥ ውኃ ደህነንት አንጻር ሲታይ የአካባቢ ጥበቃ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ያከበረ እና መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንደተወጣ የሚቆጠር መሆኑን በማመን ክሱ ውድቅ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
አፍሪካን አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ ሆልዲንግ የተሰኘው እና በተለምዶ ኢትዮ ሊዝ እየተባለ የሚጠራው በኔዘርላንድስ የተመዘገበ ኩባንያ በኢትዮጵያ ሕጎች የተደነገጉ ግዴታዎችን እንዲያከብር ለማድረግ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎችን እንደ ኢንቨስትመንት ጥበቃ መብት ጥሰት በመቁጠር 400 ሚሊየን ዶላር በላይ ካሳ እንዲከፈለው የጠየቀበት ክስ ሌላኛው ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ይህንንም ክስ ኢትዮጵያ በውስጥና የውጭ ባለሙያዎቿ በቂ ማስረጃ የክርክር ሒደቱን በበላይነት በመምራት መርታቷን አመልክተዋል፡፡
በኔዘርላንድስ ሄግ ከተማ በተደረገው የቃል ክርክር ሒደት በሶስቱም ገላጋይ ዳኞች ተመሳሳይ የስምምነት ድምጽ የቀረበውን ክስ ውድቅ በማድረግ ለክርክር የወጣውን ወጭ 65 ከመቶ የተወሰነውን ለኢትዮጵያ እንዲከፍሉ ትዕዛዝ መሰጠቱንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የመከራከር አቅሟን በማሳደግ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እየሰራች መሆኑን ገልጸው÷ ለመላው ኢትዮጵያውያን፣ ተቋማት እንዲሁም በሒደቱ ለተሳተፉ ባለሙያዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
በታሪክ አዱኛ