ቴክ

በተሽከርካሪዎች የሚደርስን የነዳጅ ፍጆታና የአካባቢ ብክለት ለመቀነስ…

By Melaku Gedif

April 08, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተሽከርካሪዎች የሚደርስን የነዳጅ ፍጆታ እና የአካባቢ ብክለት ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው አለ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፡፡

ቲቢኬ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የነዳጅ ፍጆታን እና የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችል “ግሪን ቴክ” ቴክኖሎጂ ሥራ አስጀምሯል፡፡

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አስፋው ሀዱሽ እንዳሉት÷ የአየር ብክለት መንስኤዎችን በመለየት ምቹ ከባቢን ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ለአካባቢ ብክለት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ተግባራትን ለመቆጣጠር መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመው÷ ይህም ብክለትን በመቀነስ የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ያለመ ነው ብለዋል።

በዚህ ሒደት ውስጥ ቲቢኬ አስፈላጊውን መሥፈርት በማሟላት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ይዞ ማምጣቱ የገለጹት አቶ አስፋው ÷ቴክኖሎጂው ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት የብቃት ማረጋገጫ ፍተሻ እንደተደረገበት አረጋግጠዋል፡፡

የመኪና ባለቤቶች የተሽከርካሪዎቻቸውን የጋዝ ልቀት መጠን ለመቀነስ የሚረዱ መሰል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለአካባቢ ብክለት የሚኖራቸውን አሉታዊ ተጽእኖ እንዲቀንሱ ጥሪ ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የቲቢኬ ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቶሌራ አስፋው በበኩላቸው ÷ በሀገሪቱ የሚገኙት ተሽከርካሪዎች ከኢኮኖሚ እና ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አዲሱ ቴክኖሎጂ ከ15 እስከ 30 በመቶ የነዳጅ ፍጆታ ወጪን ለመቀነስ እንዲሁም በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከ80 እስከ 96 በመቶ ለመቀነስ ያስችላል ነው ያሉት።

ድርጅቱ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ በማግኘት ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ብቁ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ንጹህ፣ አረንጓዴ እና ለኑሮ ምቹ የሆነች ሀገር ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት በእጅጉ እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል፡፡