አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪ ኤግዚም ባንክ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ምክንያት በአፍሪካ እና ካሪቢያን ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል የ10 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አጽድቋል።
ባንኩ “ገልፍ ክራይሲስ ሪስፖንስ ፕሮግራም” በሚል ያጸደቀው የድጋፍ ፕሮግራም በዓለም አቀፍ ንግድ በተለይም የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ያስከተለውን የኢኮኖሚ መዋዥቅ ለመቀልበስ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
መሰረታዊ ሸቀጦች በተለይም ነዳጅ፣ ጋዝ፣ የምግብ አቅርቦት፣ ማዳበሪያ እና መድኃኒት ያሉ አስፈላጊ ምርቶች አቅርቦት እንዳይቋረጥ የአጭር ጊዜ የውጭ ምንዛሪና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የፕሮግራሙ ዋነኛው ትኩረት እንደሆነም ተመላክቷል።
በጦርነቱ ሳቢያ ለተዳከሙ የቱሪዝምና አቪዬሽን ዘርፎች አስቸኳይ እገዛ መስጠት፣ የአፍሪካ የኢነርጂና የጥሬ ዕቃ ላኪዎች በዓለም ገበያ ካለው የዋጋ ጭማሪ ተጠቃሚ እንዲሆኑና የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የንግድ ፋይናንስ ማቅረብ በፕሮግራሙ ትኩረት ተሰጥቶበታል።
የባንኩ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤሎምቢ (ዶ/ር)÷ ድጋፉ የአፍሪካ ሀገራት አሁን ያለውን ቀውስ በሰላም እንዲሻገሩና በቀጣይ ለሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች ዝግጁ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል ብለዋል።
ባንኩ ከዚህ ቀደም በኮቪድ-19 እና በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት መሰል ድጋፎች ማድረጉን አስታውሰው÷ የአሁኑ ፕሮግራምም በግጭቱ ምክንያት የተስተጓጎሉ የኃይል፣ የወደብ እና የሎጂስቲክስ ግንባታዎችን በማፋጠን የኢኮኖሚ ጥንካሬን መገንባት የሚያስችል እንደሆነ አመልክተዋል።
ባንኩ የ10 ቢሊየን ዶላር ድጋፉን ከተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከሌሎች ቀጣናዊ ተቋማት ጋር በመተባበር ተግባራዊ እንደሚያደርገው ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ ገልጿል።
በሶስና አለማየሁ