አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በትንሳኤ በዓል ገበያ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ እየተወሰደ ነው አለ የከተማዋ ንግድ ቢሮ፡፡
የቢሮው ሃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ እንዳሉት ÷ ለትንሳኤ በዓል የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይከሰት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በከተማዋ ስድስት የግብርና ምርት ማዕከላት፣ በ246 የቅዳሜና እሑድ ገበያዎች እንዲሁም በ11ባዛሮች ላይ የበዓል መሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች ለሕብረተሰቡ እየቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የትንሳኤ በዓል ገበያው በጥሩ ሁኔታ እንዲሳለጥም አስፈላጊው የቁጥጥር ሥራ እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ቢሮው በተለያዩ የገበያ ማዕከላት ላይ ለሸቀጦች የዋጋ ተመን በማውጣት ቁጥጥር እያደረገ እንደሆነ መናገራቸውን ቢሮው ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በዚህ መሰረትም ለትንሳኤ በዓል በተዘጋጁ የገበያ ማዕከላት ውስጥ ከተቀመጠው የዋጋ ተመን በላይ ሲሸጡ በተገኙ ሰባት የንግድ ድንኳኖች ላይ ርምጃ መወሰዱን አረጋግጠዋል፡፡
ሰባቱ የንግድ ድንኳኖች ከሥራ የታገዱ ሲሆን ÷ ዳግም በመሰል የገበያ አማራጮችና ባዛሮች ላይ እንዳይሳተፉ መወሰኑንም አመልክተዋል፡፡
በመዲናዋ ለትንሳዔ በዓል በቂ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት መኖሩን ያነሱት ወ/ሮ ሀቢባ÷ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ አስፈላጊው ርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
ነዋሪዎች በትንሳኤ ገበያ ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ወይም ሕገ ወጥ ተግባር ሲያጋጥማቸው በ8588 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።