ፋና ስብስብ

ጉልባን …

By Adimasu Aragawu

April 09, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰሙነ ሕማማት አራተኛው ዕለት ጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን እራት የበላበት እና እግራቸውን በትሕትና ያጠበበት ነው፡፡

ዕለቱ በተለያዩ ስያሜዎች ማለትም፤ “ጸሎተ ሐሙስ”፣ “ትእዛዘ ሐሙስ”፣ “ሥርዓተ ሐሙስ (የምስጢር ቀን)”፣ ህፅበተ ሐሙስ፣ “የሀዲስ ኪዳን ሐሙስ” እና “የነጻነት ሐሙስ” በመባል ይታሰባል።

ፀሎተ ሐሙስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ስለ ዓለም ድኅነት የጸለየበት፣ ሕፅበተ እግር ትሕትናን ለማስተማር የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ለድኅነተ ዓለም የሚሆን አዲሱ ኪዳን የተመሰረተበት ቀን ነው።

እንዲሁም ምስጢረ ቁርባን (ሥርዓተ ሐሙስ) ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን የሰጠበት፣ የነፃነት ሐሙስ የሰው ልጅ ከኃጢአት ባርነት ነፃ የወጣበትን የምስጢር መንገድ አሳይቶበታል።

ትእዛዘ ሐሙስ “እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና” (ዮሐ.13:15) እንዲሁም “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” (ዮሐ.15:34) ብሎ አዲስ ትእዛዛትን የሰጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡

በዕለቱ ሕጽበተ እግር፣ ቅዳሴ እና የማዕድ (ጉልባን) ሥርዓቶች ይከናወናሉ።

በስርዓተ ሕፅበተ እግር ሊቀ ጳጳሱ ወይም የደብሩ አስተዳዳሪ የጌታን ትሕትና አብነት በማድረግ የካህናቱንና የምእመናንን እግር በወይንና በውኃ የሚያጥቡ ሲሆን፤ የኢየሱስ ክርስቶስን በመከራ ውስጥ ማለፍን ለማሰብ ድምፅ (ቃጭል) ሳይሰማ ሥርዓተ ቅዳሴ ይከናወናል።

ሌላው የዕለቱ ሥርዓት የማዕድ (ጉልባን) ሥርዓት ሲሆን ቂጣ እና ጉልባን ይበላል፤ ይህም እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን እና ለጊዜው ቶሎ የሚደርሰው ምግብ በመሆኑ ያንን እንደሚበሉ የሚያወሳ ነው፡፡

የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣም ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፤ ይህም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ሁሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ያለመ መሆኑ ይገለጻል።

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅ ንፍሮ ነው፡፡