የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ከፍተኛ ሥራ እያከናወነች ነው – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

By sosina alemayehu

April 10, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ከፍተኛ ሥራ እያከናወነች ነው አሉ።

ሚኒስትሩ በቪዬና በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኢነርጂና አየር ንብረት ፎረም ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ከፍተኛ ሥራ እየሠራች ነው ብለዋል።

ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስፋፋት ከ95 በመቶ በላይ ንፁህ ኃይል የማመንጨት ተግባር እየከወነች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኦኮኖሚ ልማት ላይ ያላትን ቁርጠኛ አቋም አስገንዝበዋል።

አፍሪካ ያላትን ሰፊ የታዳሽ ኢነርጂ እምቅ አቅም በመጠቀምና በወሳኝ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሸጋገር እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል።

የኢነርጂ ተደራሽነት ውስንነት፣ የመሠረተ ልማት ክፍተቶች እና የገበያ ተደራሽነት እጥረትን ጨምሮ ያሉ እንቅፋቶችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት።

ሚኒስትሩ ከፎረሙ ጎን ለጎን ከደቡብ ሱዳን እና ኦስትሪያ አቻዎቻቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።