የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

By Adimasu Aragawu

April 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!

የትንሣኤ በዓል በክርስቲያኖች ዘንድ ልዩ ቦታ ያለው በዓል ነው። ሞት የተሻረበትና ሕይወት ዋስትና ያገኘበት ነው። ከሞት ባሻገር ሕይወት፣ ከመቃብር ባሻገር ትንሣኤ መኖሩ የታወጀበት ነው። ሞት መጨረሻ መቃብር መዳረሻ አለመሆናቸው የተረጋገጠበት ነው። በአዳም ምክንያት ወደ ምድር የወረደው ሰው፣ በክርስቶስ ምክንያት ወደላይ የወጣበት ነው።

የዘንድሮውን ትንሣኤ የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ በሚያልፍ ፈተና ውስጥ እንዳለች እያሰብን ነው። መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን። ብርሃን እንዳናይ የሚጋርዱ፣ በጥልቁ ጨለማ ጠፍተን እንድንቀር አሥረው ለመያዝ የሚሞክሩ ወጥመዶች ብዙ ናቸው። ወደ ተስፋ ምድር እንዳንሻገር የሚጎትቱ ሰበቦች ሞልተዋል። ዳሩ ግን ከሕማማቱ ወዲያ ትንሣኤ፣ ከዕንቅፋቱ ባሻገር ስኬት እንደሚጠብቀን አምነን እንታገላለን።

በትንሣኤው ዋዜማ – ርግጠኞች፣ ተስፈኞች፣ ተስፋ ቆራጮች፣ ወሬኞች፣ ተስፋ አስቆራጮች፣ ተጠራጣሪዎች ነበሩ። ርግጠኞቹ የሕማማቱ ፈተና እንደሚያልፍ ርግጠኞች ነበሩ። የዕለተ ስቅለት መከራ፣ለዕለተ ትንሣኤ ዋዜማ ለመሆኑ ርግጠኞች ነበሩ። የድንጋዩ በር፣ የበሩ ማኅተም እና የመቃብሩ ጠባቂዎች ትንሣኤውን እንደማያስቀሩት ርግጠኞች ነበሩ። የሚናፈሰው ወሬ እና የሚሠራጨው አሉባልታ እድሜው አጭር መሆኑን ርግጠኞች ነበሩ። ርግጠኞችም ስለሆኑ መሥዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁዎች ነበሩ። እውነቱን ለመመስከር ቆራጦች ነበሩ። በመስቀሉ ሥር ለመገኘት ደፋሮች ነበሩ።

ተስፈኞቹ የርግጠኞቹን ያህል ሳያዩ የሚያምኑ አልነበሩም። ግን አንዳች መልካም ነገር ይጠብቁ ነበር። የተሰጠውን ትምህርት፣ የተደረገውን ተአምራት ሰምተዋል፤ አይተዋል፤ አንዳች ነገርም ጠብቀዋል። ነገር ግን ተገቢውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁዎች አልነበሩም። እውነትን ለመድፈር ቆራጦች አልነበሩም። ሐሰቱን ለመጋፈጥ ዐቅም አላገኙም። ቢያንስ ግን አንደበታቸውን ከክፉ ከልክለዋል።

ተጠራጣሪዎች አጥር ላይ የነበሩ ናቸው። በጥብርያዶስ ይበላሉ፣ በጎልጎታ ይክዳሉ። በሆሳዕና ይዘምራሉ፣ በሊቶስጥራ ይሸሻሉ፡፡ ተአምር ለማየት ይመጣሉ፣መከራ ለማየት ይሳቀቃሉ፡፡ ከደስታው አውጡልኝ፣ ከመከራው ጦመኛ ነኝ የሚሉ ናቸው። ተስፋ ቆራጮች በሚያዩትና በሚሰሙት ቶሎ የሚወሰዱ ናቸው። በእውነትና በሐሰት፣ በፍርሃትና በጽናት መካከል ያለው ድንበር የጠፋባቸው ናቸው። ሕማማቱ ሲመጣ በቶሎ ወደ ትዝታ ገቡ። ሁሉንም ነገር የትናንት ታሪክ ብቻ አድርገው ወሰዱት። ሁሉንም ነገር “ልጡ የተራሰ፣ መቃብሩ የተማሰ” አድርገው ቆጠሩት።

ከግራ ከቀኝ የሚሰሙት አሉባልታ፣ ከፊት ከኋላ የሚመጣው ጫጫታ፤ ከወዲህ ከወዲያ የሚማጣው እሳት፣ ከዚህም ከዚያም የሚያዩት መዓት አስፈራቸው። ነገን አስረሳቸው። በዚህ የተነሣ ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ ተመለሱ።

ወሬኞች ድሮም ወሬ ስቧቸው የመጡ ናቸው። ምን አለ? ምን ተባለ? ብለው የተሰባሰቡ ናቸው። የሰሙትንም ያልሰሙትንም፤ የሚያውቁትንም የማያውቁትንም፤ እውነቱንም ሐሰቱንም እያደባለቁ ኢየሩሳሌምን በወሬ ሞሏት። ቢያንስ ከትንሣኤው 15 ዓመት በኋላ ወንጌሉን የጻፈው ማቴዎስ፣ እስከዚያ ዘመን ድረስ ወሬው ብዙ ተቀባይ እንደነበረው ገልጧል።

ተስፋ አስቆራጮች ዓላማቸው ሰውን ሁሉ ከትንሣኤ መንገድ ማራቅ ነበር። እነርሱም አይሄዱ፣ ሰውም አያስኬዱ። ከመጀመሪያው አልተቀበሉትም፤ በኋላም አልፈለጉትም። ብዙ ሰዎች እንደተከተሉት ሲያውቁ ደግሞ ቅናት አቃጠላቸው፤ ክፋት አንገበገባቸው። ክርስቶስን ከሰሱ፤ ራሳቸው ምስክር ሆኑ፤ በመጨረሻም ራሳቸው ፈረዱ። መቃብሩን ዘጉ፤ ጠባቂ አስቀመጡ። በማኅተም አሸጉ። ነገር፣ ያለቀና የተቆረጠ መሰላቸው።

የትንሣኤ በዓል የእነዚህን ሁሉ እውነተኛ ማንነት የገለጠ ነው። ርግጠኞች የቆራጥነታቸው ውጤት በትንሣኤ አገኙ። ተስፈኞች እንዲህ ለሚያልፍ ጊዜ ባለመጽናታቸው አዘኑ። ተስፋ ቆራጮች አሻግሮ ማየት አቅቷቸው ከቦታቸው በመጥፋታቸው ተፀፀቱ። ወሬኞች በትንሣኤው እውነት የተነሣ ያ ሁሉ ወሬ እንደ ናቡከደነፆር ሐውልት ሲፈረካከስ አዩት። ተስፋ አስቆራጮች የገደሉት ክርስቶስ ሲነሣ፣ የዘጉት መቃብር ሲከፈት፣ ያተሙት ማኅተም ሲቀደድ፣ የመደቧቸው ጠባቂዎች ሲሸሹ በዓይናቸው በብረቱ አዩ። ትንሣኤው የሚነገር ሐቅ፣ የሚታይ እውነት ሆነ። ተጠራጣሪዎች ግን አሁንም አጥራቸው ላይ ሆነው ከግራም ከቀኝም ሳይሆኑ ቀሩ።

የኢትዮጵያችንም ነገር እንዲሁ ነው። በኢትዮጵያ ለውጥ ርግጠኞች የሆኑት ዋጋ ይከፍላሉ፤ ርግጠኝነትን ፈርተው ተስፈኞች የሆኑት ቢያንስ አንደበታቸውን ከክፉ ይጠብቃሉ፡፡ ተስፋ ቆራጮች ነገን ማየት ስለሚሳናቸው መንገዳቸውን ይቀይራሉ፡፡ ወሬኞች አውርቶ አዳሪዎች በመሆናቸው የወሬ እንጀራ ይጋግራሉ። ተስፋ አስቆራጮች “ወተቱን አጥቁረው፣ ማሩን አምርረው” የዋሖችን አታለሏቸው፡፡ ተጠራጣሪዎች አንዴ ትኩስ አንዴ ቀዝቃዛ ሲሆኑ፣ ለብ ብለው ቀሩ።

ኢትዮጵያችን ግን ትንሣኤዋን እያየች ነው። መግነዙን ፈትታዋለች፣ መቃብሩን ከፍታዋለች፤ ማኅተሙን ቀዳዋለች። ወሬኞች ከመቃብር ጠባቂዎች ጋር ተማክረው የሚያወሩትን ወሬ የምትሰማበት ጆሮ የላትም። ትንሣኤዋን አይለውጠውምና። እሷ ከዚህ በኋላ የምትጠብቀው ዕርገትን ነው። የምትጓዘው ኃይል እንደሚወርድላት አረጋግጣ ነው። ወደኋላ መመለስ የለም። ሕማማት አልፏል፤ዓርብም አልፏል፤ ቅዳሜም አልፏል። ትንሣኤ መጥቷል። በትንሣኤ ሌሊት የተኙ አልሰሙ ይሆናል። በተስፋ አስቆራጮች ተታለው የሄዱ ዜናው አልደረሳቸው ይሆናል። ትንሣኤ ግን እውን ሆኗል።

ከቻላችሁ አጥር ላይ ያላችሁ ውረዱ። ተስፈኞች ርግጠኞች ሁኑ። ተጠራጣሪዎች እመኑ። ወሬኞች ከአፍ ወደ መዳፍ ተለወጡ። ምክንያቱም – ኢትዮጵያ ወደ ትንሣኤ ተቃርባለች።

የኢትዮጵያ ትንሣኤ ከሚበሰርባቸው ምዕራፎች አንዱ ግንቦት ላይ የሚካሄደው ምርጫ ነው። ትንሣኤን ያለ ሕማማት እንደማናስበው ሁሉ ዴሞክራሲንም ከውጣ ውረድ ነጥሎ ማየት አይቻልም። በዓለም ላይ በደልዳላ መንገድ ተጉዞ ዴሞክራሲን የገነባ ሀገር የለም። ዴሞክራሲና ብልጽግና ያለ ጽናት አይሳኩም። ከእኛ በፊት ዐመጻውን በትዕግሥት የመከቱ ተሻግረዋል፤ ሑካታውን በጽናት ያለፉ አሳክተዋል።

ብንመኝም ፈተናውን አናስቀርም፤ መጽናት ግን እንችላለን። ከድህነት መውጫው ብርታታችን፣ ወደ ዴሞክራሲ መድረሻችው ትዕግሥታችን እንደሆነ አምነን ለኢትዮጵያ ትንሣኤ በሙሉ ልባችን እንትጋ!!

በድጋሚ መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንልን። ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!! ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ! ሚያዝያ 03 ቀን 2018 ዓ.ም